ሪፖርት | ሐይቆቹ ተከታታይ ድላቸውን ሲያሳኩ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ንግድ ባንክ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ሐይቆቹ ተከታታይ ድላቸውን ሲያሳኩ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ንግድ ባንክ ነጥብ ተጋርተዋል

በሁለተኛ ቀን አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ሜዳ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማ ከመመራት ተነስቶ ሸገር ከተማን ሲያሸንፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1ለ1 ተለያይተዋል።

ሸገር ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

እምብዛም አደገኛ የሚባሉ ሙከራዎች ባልተመለከትንበት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በተደረገ በእለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች ይበልጥ ወደፊት ሄደው ቀዳሚ የመሆን እድላቸውን ለማመቻቸት ሳጥን ውስጥ ሲገቡ የተስተዋሉ ቢሆንም ትልቅ የሚባል እድል ሳይፈጥሩ ቀርተው ጨዋታው 27ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ወደፊት በመሄድ ደካማ በነበሩት በተጋጣሚዎቻቸው ግብ አስተናግደዋል። ሸገር ከተማዎች በረጅም ኳስ ከሐይቆቹ ሜዳ ክፍል ደርሰው ናትናኤል ኳሱን ወደ ሳጥን ሲያሻግር አንተነህ ተፈራ ለግብ የመታው ኳሱ ተጨርፎ ያሬድ መኮንን አግኝቶ ኳስና መረብ አገናኝቷል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ሐይቆቹ የአቻነት ግብ ፍለጋ የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ የጨዋታ ብልጫ ወስደው በጌታነህ ከበደ አማካኝነት ብዙም ፈታኝ ያልሆኑ ሙከራ አድርገዋል። ነገር ግን ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው አጋማሹ ተገባዶ ወደ መልበሻ አምርተዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ የመጀመሪያ አጋማሽ ጥንካሬያቸውን ያስቀጠሉት ሐይቆቹ ከብዙ ሙከራ በኋላ 61ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አግኝተዋል። ከማዕዘን የተሻማውን እና የሸገር ከተማ ተከላካዮች በግንባር ገጭተው ያራቁትን ኳስ ያሬድ ብሩክ አግኝቶ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ ወደ ግብ በመምታት መረብ ላይ አሳርፎ አቻ ካደረጋቸው በኋላ 68ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም በላይ ከራሳቸው ሜዳ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ሽመልስ በቀለ በፍጥነት ደርሶ ሳጥን ውስጥ ደርሶ ከባህሩ ነጋሽ ጋር ተገናኝቶ ባህሩ ሲያግድበት ኳሱ ብዙ ከሳጥን ሳይርቅ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ጌታነህ ከበደ ጋር ኳሱ ደርሶ ግቡ ክፍት መሆኑን በሚገባ በመመልከት ኳሱን መረብ ላይ አሳርፎ መሪነቱን እንዲረከቡ አስችሏቸዋል። ሸገሮ መጠናቀቂያ ላይ አስቆጪ የሚባሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻሉ ቢሆንም ከመመራት ተነስተው መምራት የቻሉት ሐይቆቹ ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ወደኋላ አፈግፍገው በመከላከላቸው ግብ ሳያስቆጠሩ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ሁለቱን የአዲስ አበባ ቡድኖችን ያገናኘው ሁለተኛው ጨዋታ ፈረሰኞቹ የጨዋታ ብልጫ ከግብ ፍለጋ ጋር ያደረጉበት የነበረ ሲሆን ንግድ ባንኮች በአንፃራዊነት የፈረሰኞቹን ፈተና ከመቋቋም ባለፈ ወደ ፊት የመሄድ አጨዋወታቸው ጥሩ ሳይሆን ቀርቶ ከተደጋጋሚ መከላከል በኋላ ግብ አስተናግደዋል። 34ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ዮሐንስ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ የአብስራ ጎሳዬ በግሩም መጀመሪያ ንክኪ ኳሱን አመቻችቶ ለሀብታሙ ጉልላት አሻግሮለት ኳስና መረብ በማገናኘት ፈረሰኞቹን መሪ አድርጓቸዋል። ተጨማሪ ግቦችን ለማስመልከት የቀረቡበት የሶስተኛ ሜዳ ክፍል እንቅስቃሴዎችን ተመለክተናል። ፈረሰኞች በቆመ ኳስ ካደረጉት ሙከራ በኋላ ብርሃኑ አሻሞ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ ተጠቃሽ ነበር። ንግድ ባንክ ጨዋታው 40ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ በፊልሞን ገብረጻድቅ አማካኝነት ብቸኛ ወደግብ የቀረበ በግንባር የተደረገ ሙከራ አድርገው ግብ ጠባቂው አግዶባቸው አጋማሹ ተገባዷል።

በመጠኑ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተሻሽለው የቀረቡ በሚመስለው በሁለተኛው አጋማሽ አልፈው አልፈው የአቻነት ግብ ፍለጋ ማነፍነፋቸውን ይቀጥሉ እንጂ ፈረሰኞቹ በፈጣን ሽግግር ሳጥን እየደረሱ አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ጨቃኝ መሆን ተስኗቸው ሲቸገሩ እያስተዋልን 75ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ ተቆጥሮባቸዋል። የቆመ ኳስ አዲስ ግደይ አስጅምሮ የተሻማውን ኳስ ናትናኤል ዳንኤል በተከላካዮች መካከል ሾልኮ በመውጣት ግብ ጠባቂው ተረጋግቶ ለመያዝ ጥረት ሲያደርግ ኳሱን ቀድሞ በግንባሩ አግኝቶ ወደ ግብነት ቀይሮታል። ከአቻነት ግብ በኋላ ፈረሰኞቹ ዳግሞ መሪ ለመሆን የቀረበ አደገኛ ሙከራ በቆመ ኳስ ብርሃኑ አሻሞ አድርጎ ለጥቂት ከፍ ብሎ ካለፈባቸው ከደቂቃዎች በኋላ ድጋሚ የቆመ ኳስ ቢኒያም ፍቅሩ አክርሮ መትቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አማኑኤል ደስታ አግዶባቸዋል።

ጨዋታ መጠናቀቂያ ላይ የፈረሰኞች የፊት መስመር ተጫዋች  ቢኒያም ፍቅሩ የንግድ ባንኩን ተከላካይ ያሲንን በማታት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ የተወገደበት ክስተት ሲጠቀስ ሁለት ግቦችና አንድ ቀይ ካርድ የታየበት ጨዋታው 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።