ጨዋታ ሳምንቱ መጨረሻ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮጵያ መድንን ከመመራት ተነስቶ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ግቦች 2ለ1 አሸንፏል።

የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከኢትዮጵያ መድን አገናኝቷል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፈጣን ማጥቃት እንቅስቃሴ ጨዋታውን የጀመረ ሲሆን ሶስተኛው ደቂቃ ላይ ሳይመን ፒተር ርቀት ላይ ሆኖ ካደረገው ሙከራ በኋላ ናትናኤል ዳንኤል የቆመ ኳስ አግኝቶ ግልፅ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ አምክኖ ከደቂቃዎች በኋላ ሳይመን ፒተር በድጋሚ ኳስ እየገፋ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ከፋሲል ገብረሚካኤል ጋር ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው በግሩም ቅልጥፍና ኳሱን አግዶባቸዋል። ወደግብ በመቅረብ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ንግድ ባንኮች 19ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም ከሳጥን ውጭ የተደረገ አደገኛ ጠንከር ያለ ሙከራ በዛብህ ካቲሶ አማካኝነት አድርገው ከግቡ ቋሚ ብረት ለጥቂት ርቆ ያለፈባቸው አጋጣሚ ይጠቀሳል።
በአንፃራዊነት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተወሰደባቸው ኢትዮጵያ መድኖች ምንም እንኳን ወደፊት በመሄድ አኳያ ደካማ የነበሩ ቢሆንም በግራ መስመር በኩል እየገቡ አደጋ ለመፍጠር ጥረት አድርገው በአንድ አጋጣሚ ሳይጠበቅ የተገኘውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይረው መሪ ሆነዋል። የአጋማሹ አካፋይ ላይ ወገኔ ገዛኸኝ በግራ መስመር በኩል ሆኖ ያሻማውን ኳስ ረመዳን የሱፍ በጠባብ አንግል በግንባሩ ገጭቶ ኳስና መረብ አገናኝቷል።

በኳስ ንክኪ ብልጫ እንዲሁም እድሎችን እየፈጠሩ ግብ ጠባቂውን መፈተሽ የቀጠሉት ንግድ ባንኮች ግብ ካስተናገዱ በደቂቃዎች ልዩነት አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ሳጥን ውስጥ ገብተው ያደረጉት አስቆጪው ሙከራ ሲጠቀስ 24ኛው ደቂቃ ላይ ሳይመን ፒተር ኳስ በራሱ ጥረት እየገፋ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ያደረገውን ሙከራ ተደጋጋሚ በጥሩ ሁኔታ ኳሶችን ሲያድን የነበረው ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል አግዶባቸዋል።
በረጃጅም ኳሶች እየገቡ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሲቀርቡ የነበሩት መድኖች የአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ ዳዊት አውላቸው መሬት ለመሬት በግሩም እይታ ያቃበለውን ኳስ ረመዳን የሱፍ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው አማኑኤል ደስታ እንዴትም ባያግድባቸው መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገው በእፎይታ ወደ መልበሻ ክፍል ሊገቡ የቀረቡበት ጥራት ያለው ሌላኛው ሙከራ ሆኖ አጋማሹ ተጠናቆ ወደ እረፍት አምርተዋል።

የመጀመሪያ አጋማሽ ጥንካሬያቸውን በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ አጠናክረው የተመለሱት ንግድ ባንኮች ከተደጋጋሚ ጥረቶች በኋላ ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። 52ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ በግራ መስመር ሆኖ ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል በቀላሉ ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርግ ናትናኤል ዳንኤል ከእጁ ነጥቆ በቀላል ንክኪ ወደ ግብነት ቀይሮ ወደ ጨዋታ የመለሰቻቸውን ግብ ካስቆጠር ከአስር ደቂቃ ቆይታ በኋላ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። አዲስ ግደይ ከብሩክ ብፁዕአምላክ ጋር ባደረጉት ጥሩ ጥምረት ብሩክ በተከላካዮች መካከል ከፍ አሾልኮ የሰጠውን ኳስ አዲስ ግደይ በግሩም ፍጥነት እና ብልሃት ኳስ አግኝቶ በፍፁም መረጋጋት ማስቆጠር ችሏል።
ቢኒያም ካሳሁንን 73ኛው ደቂቃ ላይ አለን ካይዋ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ አትተው ከጭማሪ ደቂቃዎች ጋር ከሃያ አምስት ደቂቃ በላይ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት የተገደዱት ንግድ ባንኮች ቀሪዎችን ደቂቃዎች በመከላከል ብሎም በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግቦች ለማስቆጠር ወደፊት ሲሄዱ ያስተዋልን ሲሆን ኢትዮጵያ መድኖች በበኩላቸው ቢያንስ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ሊሳካላቸው ሳይችል ሲቀር እያስተዋልን በተለይም ጭማሪ ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ሆኖ ወገኔ ገዛኸኝ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አማኑኤል ደስታ ሳይጠበቅ ጨርፎ ያወጣባቸው ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ሲታወስ ጨዋታውም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመመራት ተነስቶ ኢትዮጵያ መድንን 2ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ተቋጭቷል።

