የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ካሳየ አራጌ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድንቅ ተጫዋች የነበው ካሳየ አራጌ እግር ኳስን ካቆመ በኋላ ወደ ስልጠናው ዓለም በመቀላል ለመጀመርያ ጊዜ በ1994 ለአምስት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡናን በማሰልጠን ጀምሮ በቀጣይ ዓመት በ1995 ቡናማዎቹን የውድድር ዓመቱን አሰልጠኖ አልፏል።
በመቀጠል ኑሮውን በሀገረ አሜሪካ ካደረገ ከረጅም ዓመት በኋላ በ2012 ዳግም ኢትዮጵያ ቡናን ለማሰልጠን የመጣ ሲሆን በቆየባቸው ሦስት ዓመታት በተለይ በ2014 ኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቁ ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ቡድኑን ለማሳለፍ ችሏል።
ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከተለያየ በኋላ ክለብ አልባ ሆኖ የቆየው አሰልጣኝ ካሳየ አራጌ ከአራት ዓመት ቆይታ በኋላ በድጋሚ ወደ ሀገር ቤት ሊመጣ መሆኑን አውቀናል። የራሱ የጨዋታ ሀሳብ እንዳለው የሚነገርለት ካሳየ በዚህ ሳምንት ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጣ እና የመምጣቱ ዋና ዓላማ ዳግም ከፕሪሚየር ሊግ ክለቦች መካከል አንዱን ለመያዝ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

