ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ24ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ24ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

24ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ አራት መርሐግብሮች ይጀመራል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል

ፋሲል ከነማ ከ መቻል

በሰላሣ አራት ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች ከናፈቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ ከቅርብ ተፎካካሪያቸው ጋር ይፋለማሉ። ከአራት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ በመጨረሻው መርሐ ግብር ከሽረ ምድረ ገነት ጋር ነጥብ የተጋሩት ዐፄዎቹ ከስድስት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ሙሉ ነጥብ ለማስመዝገብ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሽንፈት ካልቀመሰው መቻል ጋር ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናሉ። ከሳምንታት በፊት ከመሪዎቹ ጎራ የነበረውና ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 18 ነጥብ ሁለቱን ብቻ ያሳካው ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ ድል አድርጎ ደረጃውን ለማሻሻል በቀደመ ጥንካሬያቸው መዝለቅ ያልቻሉትን የተከላካይ እና የፊት መስመሩን በብዙ ረገድ ማሻሻል ይጠበቅበታል።

በሰላሣ አምስት ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው መቻል ወደ መሪዎቹ ይበልጥ ለመጠጋት የሚያስችለውን ነጥብ ለማግኘት ወደ ጨዋታው ይቀርባል። በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ በወላይታ ድቻ ከደረሰበት ሽንፈት በኋላ ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች አንድ ድል እና ሁለት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገበው መቻል ወደ ሊጉ አናት ተጠግቶ በፉክክሩ ለመዝለቅ በውድድር ዓመቱ ላይ የሚስተዋልበትን የወጥነት ችግር መቅረፍ ይኖርበታል። ቡድኑ አራት ግቦች ካስተናገደበት ጨዋታ በኋላ ባደረጋቸው ሦስት መርሐ ግብሮች መረቡን አስከብሮ መውጣቱ እንደ አወንታ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም በዛሬው ዕለት ሙሉ ነጥብ ለማግኘት ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረውና ተከታታይነት ያለው ብቃት ማሳየት ያልቻለውን የማጥቃት አጨዋወቱ አካሄድ ማረም ግድ ይለዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 16 ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ 7 ጨዋታ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖራቸው መቻል 4 ጨዋታዎች አሸንፏል። ቀሪዎቹ 5 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ናቸው። ፋሲል 21 ሲያስቆጥር መቻል 12 ግቦች  አስቆጥሯል።

ሀድያ ሆሳዕና ከ ሸገር ከተማ

በሀያ ዘጠኝ ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ በታች ያሉ ቡድኖች ከስጋት ከቀጠናው ለመራቅ እያደረጉት ካለው ብርቱ ፉክክር ፈቀቅ ለማለት ዛሬ ድል ማድረግ ግድ ይላቸዋል። በሁለተኛው ዙር በተደረጉ ጨዋታዎች አንድ ድል፣ አንድ ሽንፈት እና ሁለት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡት ነብሮቹ የዛሬው ተጋጣሚያቸው በሁለት ነጥብ እና አራት ደረጃዎች ዝቅ ብሎ የተቀመጠ የቅርብ ተፎካካሪያቸው እንደመሆኑ ፍልሚያው ፈታኝ እንደሚሆን እሙን ነው። ከዚህ ወሳኝ ጨዋታ ነጥብ ልዞ ለመውጣት ደግሞ ባለፉት ስምንት መርሐ ግብሮች በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር ያልቻለውን የፊት መስመር ላይ ለውጦች ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በሀያ ሰባት ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሸገር ከተማዎች ካሉበት የወራጅ ቀጠና አፋፍ ለመራቅ የሚያስችላቸውን ነጥብ ለማግኘት ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። በመጨረሻው መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ለባዶ በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱት ሸገር ከተማዎች ሽንፈት ከቀመሱ 11 የጨዋታ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ቡድኑ እጅ ከሰጠባቸው አራት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ከሽንፈት መራቁ እንደ አወንታ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም ከአቻ ውጤቶች መላቀቅ አለመቻሉ ግን ደረጃውን እንዳያሻሽል አድርጎት ቆይቷል። በሊጉ በርከት ያሉ የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው (በጣምራ) ሸገር ከተማ ባለፈው ሳምንት ያገኘውን ወሳኝ ድል ለማስቀጠልም የፊት መስመሩን የአፈፃፀም ደረጃ ከፍ ማድረግ ይኖርበታል።

ሁለቱም ቡድኖች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ 1 ለ 1 መጠናቀቁ ይታወሳል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ባህር ዳር ከተማ

አንድ ቀሪ ጨዋታ እያላቸው በሀያ አምስት ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናሉ። ድሬዳዋ ከተማን አራት ለባዶ ከረመረሙበት የ15ኛ ሳምንት ጨዋታ በኋላ በተደረጉ ሰባት መርሐ ግብሮች አራት ሽንፈቶች እና ሦስት የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ከድል ጋር የተራራቁት ፈረሰኞቹ በቅርብ ሳምንታት ባስመዘገቧቸው ውጤቶች ወራጅ ቀጠናው ላይ ገብተዋል። ለመጨረሻ ጊዜ ድል ባደረገበት 15ኛ ሳምንት በ 22 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ የነበረው ቡድኑ ከገጠመው አስከፊ መንሸራተት ለማገገም ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች 1 ግብ ብቻ ያስቆጠረውን የፊት መስመሩን ማሻሻል ግድ ይለዋል።

ሀያ ስምንት ነጥቦች ሰብስበው 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህርዳር ከተማዎች ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ፈረሰኞቹን ይገጥማሉ። ሀድያ ሆሳዕናን ካሸነፉበት የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ መርሐ ግብር በኋላ በተደረጉ ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈት እና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት የጣና ሞገዶቹ የዛሬ ጨዋታ ከወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥቦች ርቀት ላይ ሆነው የሚያደርጉት እንዲሁም ፍልሚያው በወራጅ ቀጠናው ከሚገኝ ቡድን ጋር የሚደረግ እንደመሆኑ
ወሳኝ ነው። በወሳኙ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ለማግኘትም ባለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች አራት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው እና በመጨረሻዎቹ ሦስት መርሐ ግብሮች ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻለው የማጥቃት አጨዋወታቸው ማሻሻል ይኖርባቸዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲሱ አቱላን ከጉዳት መልስ ሲያገኝ ጳውሎስ ከንቲባ ግን ለዛሬው ጨዋታም አይደርስም። የጣና ሞገዶቹ አማኑኤል ገብረሚካኤልን ከጉዳት ማንያዘዋል ካሳን ደግሞ ከቅጣት መልስ ያገኛሉ።

ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 13 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ባህር ዳር ከተማ አራት ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ሦስት ድሎችን አሳክተው ስድስት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ አሥራ አራት ባህር ዳር ከተማም በተመሳሳይ  አሥራ አራት ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ሲዳማ ቡና ከ ሽረ ምድረ ገነት

በአርባ ሁለት ነጥቦች በሊጉ አናት የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ከገጠማቸው የውድድር ዓመቱ ሦስተኛ ሽንፈት በማገገም መሪነታቸውን ለማጠናከር ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ።

ሲዳማ ቡናዎች በመጨረሻው መርሐ ግብር በወላይታ ድቻ ሽንፈት ማስተናገዳቸውን ተከትሎ ከተከታያቸው ሀዋሳ ከተማ የነበራቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ብሏል። ቡድኑ ባለፉት ጨዋታዎች ያሳየው እንቅስቃሴ ለክፉ የሚሰጥ ባይሆንም በማጥቃት አጨዋወቱ ላይ የሚታየው በቂ የጎል ዕድሎችን የመፍጠር ድክመት አካሄዱ ወጥነት የጎደለው እንዲሆን አድርጎታል። ቡድኑ ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ውስጥ በሁለቱ ብቻ ድል ማድረጉም የዚህ ማሳያ ነው። የፊት መስመራቸው  ለማጠናከር ሁለት ወሳኝ ዝውውሮችን የፈፀሙት ሲዳማ ቡናዎች ለዋንጫ የሚያደርጉትን ጉዞ ለማቃናትም ለፉክክሩ የሚመጥን ጠንካራ የፊት መስመር ማዋቀር ግድ ይላቸዋል።

ሀያ ሰባት ነጥቦች በመሰብሰብ 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሽረ ምድረ ገነቶች ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ሙሉ ነጥብ ለማስመዝገብ ከሊጉ መሪ ጋር ይፋለማሉ።

በዳንኤል ዳርጌ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ወደ ዛሬው ጨዋታ የሚቀርቡት ሽረ ምድረ ገነቶች በቅርብ ሳምንታት ባስመዘገቧቸው ውጤቶች ወደ ወራጅ ቀርበዋል።

በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ አራት ጨዋታዎች  ሽንፈት ሳይቀምስ እንዲሁም ግብ ሳያስተናግድ ዙሩን ካጠናቀቀ በኋላ ሁለት ሽንፈቶች፣ አንድ ድል እና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገበው ቡድኑ የዛሬው ጨዋታ ከወራጅ ቀጠናው በሁለት ነጥብ ርቀት ላይ ሆኖ የሚያከናውነው እንደመሆኑ ከስጋት ቀጠናው ርቆ መጠነኛ እፎይታ ለማግኘት  ነጥብ ማስመዝገብ ግድ ይለዋል። ይህ እንዲሆን ደግሞ በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች መረቡን አስከብሮ ከወጣ በኋላ በቅርብ ሳምንታት መጠነኛ መቀዛቀዝ የታየበትን የመከላከል አደረጃጀታቸው ወደ ቀድሞ ብቃቱ መመለስ ይኖርበታል።

ቡድኖቹ በሊጉ አምስት ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ አራቱን ሲያሸንፍ በአንዱ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ሲዳማ ስምንት ሲያስቆጥር ሽረ ደግሞ አራት ማስቆጠር ችሏል (የተሰረዙትን የ2012 ሁለት ጨዋታዎች አያካትትም)።