ኢትዮጵያ ቡናዎች ከምስረታ ጀምሮ ክለቡን ያገለገሉትን መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞን በታላቅ ክብር ሊሸኙ ነው

በኢትዮጵያ ቡና ታሪክ ስማቸው በቀዳሚነት ከሚጠሩት ሰዎች መካከል ግንባር ቀደም ሰው የሆኑት እና ቡናማዎቹን ከምስረታ ጀምሮ እስከዚህ ዘመን ድረስ ለረጅም ዓመታት በፕሬዝዳንትነት እንዲሁም በተለያዩ የሀላፊነት ቦታዎች ሲያገለግሉ የቆዩት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ (ቼንቶ) በቅርቡ ክለቡን በይፋ ተሰናብተው በምትካቸው አቶ እስራኤል ደገፉ (ዶክተር)) በፕሬዝደንትነት መሾማቸው ይታወቃል።
ታዲያ ክለቡን ለረጅም ዓመታት በከፍታውም ሆነ በዝቅታው አብረውት የዘለቁት ታላቁን ሰው ነገ በክብር ሊሸኙ እንደሆነ ሰምተናል። በ26ኛ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ከሸገር ከተማ ጋር ነገ 7፡00 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከሚያከናውነው ጨዋታ አስቀድሞ ከስድስት ሰዓት ጀምሮ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የክለቡ የልብ ደጋፊዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት የመሸኛ ፕሮግራም እንደሚዘጋጅላቸው እና አዲሱን የክለቡን ፕሬዝደንት አቶ እስራኤል ደገፉን (ዶክተር) እንደሚስተዋወቁ አውቀናል።
የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊም ሆነ የስፖርት ቤተሰብ በዕለቱ ተግኝቶ እኝህ ታላቅ የኢትዮጵያ እግርኳስ ሰው በክብር እንድሸኝ ክለቡ ጥሪውን ቀርቧል። በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ያለፉትን ስድስት ዓመት እራሱን ችሎ እየተዳደረ የሚገኘውን የሊጉ አክስዮን ማህበርን በፕሬዝደንትነት እየመሩ እንደሆነም ይታወቃል።

