ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ26ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ26ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

26ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ አራት ጨዋታዎች ይጀመራል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል

ኢትዮጵያ ቡና ከ ሸገር ከተማ

አንድ ቀሪ ጨዋታ እያላቸው በ35 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ሰንጠረዡ ወገብ የሚያስጠጋቸውን ድል ፍለጋ ሸገር ከተማን ይገጥማሉ።

በመጨረሻው ሳምንት በቢንያም ጌታቸው ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ መድንን ማሸነፍ የቻሉት ቡናማዎቹ በሁለተኛው ዙር የሚታይ መሻሻል አስመዝግበዋል። በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ድል አድርጎ አንድ ሽንፈት በማስተናገድ ማግኘት ከሚገባው አስራ አምስት ነጥብ አስራ ሁለቱን ያሳካው ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ባስመዘገባቸው ውጤቶች ከነበረበት የስጋት ቀጠና መውጣት ችሏል። በያዘው የድል ጎዳና ለመዝለቅም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን ማስቆጠር የቻለው የማጥቃት ጥንካሬውን ማስቀጠል ይኖርበታል።

በሰላሣ ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሸገር ከተማዎች ካሉበት የስጋር ቀጠና ለመራቅ ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው።

በ25ኛው ሳምንት ከአስራ ሁለት ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች በኋላ በአርባ ምንጭ ከተማ ሽንፈት ያስተናገዱት ሸገር ከተማዎች በወራጅ ቀጠናው መውጫ ላይ ከተቀመጠው ቡድን ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ሁለት ብቻ መሆኑን ተከትሎ ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ በዛሬው ጨዋታ ድል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ጨዋታው በጥሩ ወቅታዊ አቋም ከሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ጋር እንደመሆኑ ፈተናው ቀላል ባይሆንላቸውም ሙሉ ነጥብ ለማግኘት በሁለተኛው ዙር በጥሩ የግብ ማስቆጠር ብቃት ላይ የሚገኘው የተጋጣሚያቸው የፊት መስመር እንቅስቃሴ መግታት እንዲሁም የሚስተዋሉባቸው የአፈፃፀም ክፍተቶችን ማረም ይኖርባቸዋል። 

በኢትዮጵያ ቡና በኩል ያለው የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ መቐለ 70 እንደርታ

ሰላሣ አንድ ነጥብ ሰብስበው 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ከምዓም አናብስት ጋር ይፋለማሉ። በመጨረሻው ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ የተጋራው ቡድኑ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥብ በመሰብሰብ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል። ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች መልስ ድሬዳዋ ከተማ እና ጠንካራው ሀዋሳ ከተማን አሸንፈው ከወላይታ ድቻ ጋር አቻ የተለያዩት ንግድ ባንኮች በዛሬው ጨዋታ ድል ለማድረግ በሁለት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ካስቆጠረ በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ የተቀዛቀዘውን የማጥቃት አጨዋወታቸው ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል።

በሀያ ሦስት ነጥብ 19ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት ዕድላቸውን ለማለምለም ወደ ዛሬው ጨዋታ ይቀርባሉ። በመጨረሻው ሳምንት በሲዳማ ቡና ሽንፈት ያስተናገዱት ምዓም አናብስት ሽረ ምድረ ገነትን ካሸነፉበት የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ መርሐ ግብር በኋላ ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈት እና ሁለተ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ከድል ጋር ተራርቀዋል። ከዚህ ድል አልባ ጉዞ ለመውጣት ሁለንተናዊ ለውጥ ማድረግ የሚጠበቅበት ቡድኑ በዛሬው ጨምሮ በቀጣይ ወሳኝ መርሐ ግብሮች ነጥብ ለማስመዝገብ በተለይም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረውን የማጥቃት አጨዋወቱ ማሻሻል ግድ ይለዋል።

መቐለ 70 እንደርታዎች አሸናፊ ሀፍቱን በህመም ምክንያት አያሰልፉም፤ ቅጣት ላይ የነበሩት ፍፁም ዓለሙ፣ ተመስገን ተስፋዬና አብዲ ዋበላ እንዲሁም አዲስ ፈራሚዎቹ አይባሚ ፕሪንስ እና ዓብዱለጢፍ ባምባ ግን ለጨዋታ ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች ባደረጓቸው 3 ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1 ድል ሲያስመዘግብ የተቀሩት 2 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። በጨዋታዎቹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3 መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ 2 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

አንድ ቀሪ ጨዋታ በእጃቸው ይዘው በሀያ ስምንት ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናሉ።

በ25ኛው ሳምንት ከስምንት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ሀድያ ሆሳዕናን ሁለት ለአንድ አሸንፈው ከድል ጋር የታረቁት ፈረሰኞቹ ማግኘት ከሚገባቸው ሀያ አራት ነጥቦች ውስጥ ሦስቱን ብቻ ካሳኩበት አስከፊው የስምንት ሳምንታት ጉዞ በተከታታይ ድሎች ለማገገም በጥሩ ወቅታዊ አቋም ከሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ይፋለማሉ። ተጋጣሚያቸው በሁለተኛው ዙር ይበልጥ ተጠናክሮ የቀረበ እና በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ የሚገኝ ቡድን እንደመሆኑ ቀላል ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ ባይገመትም ድል ባደረጉበት ጨዋታ ላይ በሁለቱም አጋማሾች የነበራቸው ብልጫ ማስቀጠል እንዲሁም በስምንት መርሐ ግብሮች አንድ ግብ ብቻ በማስቆጠር ደካማ ጉዞ ካደረገ በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር የቻለውን የማጥቃት አጨዋወታቸውን ይበልጥ ማጠናከር ከጨዋታው አንዳች ነገር ይዘው እንዲወጡ ያስችላቸዋል ተብሎ ይገመታል።

በሰላሣ ስምንት ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ወደ ዋንጫ ፉክክሩ የሚቀላቅላቸውን ሦስት ነጥብ ለማግኘት ወደ ዛሬው ጨዋታ ይቀርባሉ።

ከ16ኛው እስከ 21ኛው ሳምንት ድረስ በተካሄዱ ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ሦስት ሽንፈት እና የአቻ ውጤቶች በእኩሌታ በማስመዝገብ ድል ሳያደርጉ ከዘለቁ በኋላ ባለፉት አራት ሳምንታት ወደ ጥሩ ብቃት የመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በቅርብ ሳምንታት በሁሉም ረገድ አወንታዊ ለውጦች አስመዝግበዋል። ቡድኑ ሦስት ተከታታይ ድሎች ካስመዘገበ በኋላ በመጨረሻው ሳምንት ከባህርዳር ከተማ ጋር ነጥብ መጋራት ቢችልም በቅርቡ በተለይም በማጥቃቱ ረገድ ያሳየው መሻሻል አስደናቂ ነው፤ ቡድኑ ኳስና መረብ ማገናኘት ካልቻለባቸው አምስት መርሐ ግብሮች በኋላ በሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ማስቆጠሩ እንዲሁም በየጨዋታዎቹ የሚፈጥራቸው ዕድሎችም የዚህ ማሳያ ናቸው። ቡድኑ ከአንድ ጨዋታ መልስ ዳግም ወደ ድል መንገድ ተመልሶ የዋንጫ ፉክክሩን ለመቀላቀልም የተጠቀሰውን ጠንካራ ጎኑ ማስቀጠል ይኖርበታል።

ሁለቱ ቡድኖች 43 ጊዜ ሲገናኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ 30 በማሸነፍ  የበላይነትን ሲይዝ ኤሌክትሪክ 4 አሸንፎ በ9 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 71 ግቦች ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ በበኩሉ 30 አስቆጥሯል።

ሽረ ምድረ ገነት ከ ድሬዳዋ ከተማ

ሀያ ስምንት ነጥብ ሰብስበው 18ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሽረ ምድረ ገነቶች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በአንድ ነጥብ እና ሦስት ደረጃዎች ልቆ ከተቀመጠው ድሬዳዋ ከተማ ይፋለማሉ።

የመጀመሪያውን ዙር 12ኛ ደረጃን ይዘው ካጠናቀቁ በኋላ ባለፉት ስድስት ሳምንታት ባስመዘገቧቸው ውጤቶች ወደ ወራጅ ቀጠናው ለመግባት የተገደዱት ሽረ ምድረ ገነቶች ካለው የነጥብ መቀራረብ እንዲሁም ከተጋጣሚያቸው ጋር ባላቸው የነጥብ ልዩነት አንፃር ዛሬ የሚደርጉት ጨዋታ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሚያደርጉት ጉዞ  ወሳኝ ነው። ከዚህ ወሳኝ መርሐ ግብር ነጥብ ይዞ ለመውጣትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀዛቀዘ የመጣው የቡድኑ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ጥንካሬ መመለስ እንዲሁም በመጀመሪያው ዙር

የመጨረሻ አራት ጨዋታዎች መረቡን በማስከበር
በጥሩ ብቃት ከዘለቀ በኋላ በሁለተኛው ዙር በስድስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦችን ያስተናገደው የተከላካይ ክፍሉን ማሻሻል ግድ ይለዋል። 

በሀያ ዘጠኝ ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ካሉበት የስጋት ቀጠና ለመራቅ ከቅርብ ተፎካካሪያቸው ሽረ ምድረ ገነት ጋር ይፋለማሉ።

በመጨረሻው ጨዋታ ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ወደ ዛሬው ጨዋታ የሚቀርቡት ብርቱካናማዎቹ ከተጋጣሚያቸው ጋር በተመሳሳይ በሁለተኛው ዙር ባስመዘገቡት ውጤት ለገጠማቸው የደረጃ ማሽቆልቆል ምላሽ ለመስጠት ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈት፣ ሁለት አቻ እና አንድ ድል ያስመዘገበው ቡድኑ ከዚህ አካሄድ ለመውጣትም ዘርፈ ብዙ መሻሻሎችን ማድረግ ይጠበቅበታል። ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦችን ያስተናገደው የተከላካይ መስመራቸው አንገብጋቢ ለውጥ የሚሻ ክፍል ሲሆን በሊጉ ከመቐለ 70 እንደርታ ቀጥሎ ጥቂት ግቦች በማስቆጠር ከሌሎች ሦስት ክለቦች ጋር በጣምራ
ሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው የማጥቃት ክፍላቸውም
ሌላው መሻሻል የሚገባው የቡድኑ ክፍል ነው።

ሽረ ምድረ ገነቶች በዛሬው ጨዋታ አንተነህ ተስፋዬ፣ ቢንያም ላንቃሞ እና ፀጋይ ፀሐዬን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም፤ ቅጣት ላይ የነበሩት ሬችሞንድ አይ እና አዲስ ተስፋዬ እንዲሁም ጉዳት ላይ የነበረው ዳንኤል ዳርጌ ግን ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።

በ2011 ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት ቡድኖቹ ከተሰረዘው እና የአቻ ውጤት ከተመዘገበበት የ2012 ጨዋታ ውጭ 5 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ በሦስቱ ጨዋታዎች ነጥብ ሲጋሩ ሁለቱም በተመሳሳይ አንድ አንድ ጨዋታ አሸንፈዋል። በግንኙነቱ ሁለቱም በተመሳሳይ ስድስት ግቦችን አስቆጥረዋል።