ኢትዮጵያ ቡና እና ሸገር ከተማ 1-1 ሲለያዩ ፈረሰኞቹ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ በ2ለ1 ውጤት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ድል ማድረግ ችለዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ሸገር ከተማ
በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የነበረ የኳስ እንቅስቃሴን ባስመለከተን አጋማሽ 3ኛው ደቂቃ ላይ ሸገር ከተማዎች በቡልቻ ሹራ አማካኝነት እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራን ማድረግ የቻሉ ሲሆን ለጥቂት በግብ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶባቸዋል።
የአጋማሹ መደበኛ የጨዋታ ሰዓት ሊጠናቀቅ ሶስት ያክል ደቂቃዎች ሲቀሩት ሸገር ከተሞች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። 42ኛው ደቂቃ ላይ መነሻውን ከቅጣት ምት ያደረገው እና የቡና ተጫዋቾች መዘናጋታቸውን ተከትሎ በፈጣን ቅልጥፍና ያስጀመሩትን ኳስ አሚር አብዶ ወደ ግብነት ቀይሮ ሸገር ከተማን መሪ ሆኖ ወደ እረፍት እንዲያመሩ አድርጓል።

ከዕረፍት መልስ 50ኛው ደቂቃ ላይ ቡናዎች በቢንያም ጌታቸው ሙከራ ቢያደርጉም የግቡን አግዳሚ ገጭቶ በመመለሱ አጋጣሚው ሳይሳካ ቀርቷል። በ61ኛው ደቂቃ ላይ የታየው ድራማዊ ክስተት የጨዋታውን መልክ ቀይሮታል የሸገር ከተማው ቡልቻ ሹራ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ በቸልተኝነት ያባከነውን ወርቃማ ዕድል ኢትዮጵያ ቡናዎች በመልሶ ማጥቃት ወደ ተቃራኒ ግብ ክልል በመድረስ በቢኒያም ጌታቸው ጥረት ኳስ በእጅ መነካቱን ተከትሎ የፍጹም ቅጣት ምት ማግኘት ችለዋል።
የጨዋታው ዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ መጀመሪያ በቢጫ ካርድ ቢያልፉትም በረዳት ዳኛው ተመስገን ሳሙኤል ጥቆማ ውሳኔያቸውን በማሻሻል ግልፅ የግብ ዕድል ሆን ብለህ በእጅህ አቋርጠሃል በሚል ገዛኸኝ ደሳለኝን በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አሰናብተዋል። የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት አቡበከር አዳሙ መትቶ ግብ ጠባቂው ባህሩ ነጋሽ ቢመልስበትም በድጋሚ የተመለሰውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡናማዎቹን አቻ አድርጓል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
አንድ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ብቻ ባስመለከተን በመጀመሪያው አጋማሽ 10ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ሀብታሙ ሸዋለም አለም የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከቡድን ጓደኞቹ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ይዞት የገባውን እና ያቀበለውን ኳስ በፈቃዱ አስረሳኸኝ በግንባሩ ገጭቶ ኢትዮ ኤሌክትሪክን መሪ ማድረግ ችሏል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶችም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በተገኑ ተሾመ የግንባር ኳስ አማካኝነት አቻ ለመሆን ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ለጥቂት በግቡ አግዳሚ ወጥቶባቸዋል።
ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ 53ኛው ደቂቃ ላይ መነሻውን ከቀኝ መስመር ከሄኖክ ዮሃንስ ያደረገውን እና በስተመጨረሻ የተሻማውን ኳስ ያገኘው ተገኑ ተሾመ ድንቅ በሆነ በራስ መተማመን እና ድንቅ በሆነ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ ፈረሰኞችን አቻ ማድረግ ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ራሳቸውን በሚገባ አሻሽለው የቀረቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 76ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ጉልላት ያሻገረውን ኳስ ፍጹም አለሙ በሚገባ ተቆጣጥሮ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከላካዮች የሰሩትን የመከላከል ስህተት ተጠቅሞ ሁለተኛ ግቡን አስቆጥሮ ቡድኑን ከመመራት ተነስቶ መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የአቻነት ግብ ለማግኘት ከፍተኛ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን በያሬድ ደማነ፣ በፓትሪክ ሲቦማኒኔ እና በኢዮብ ገብረማርያም አማካኝነት ለግብ የቀረቡ አስቆጪ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። የጨዋታው መጠናቀቂያ 90+3 ላይ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ተከላካይ ቢኒያም በቀለ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ይህንን ተከትሎ ፈረሰኞቹ ተከታታይ ድላቸውን በማሳካት አምስት ደረጃውችን በማሻሻል 12ኛ ደረጃ ተቀምጠዋል።

