በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚደረጉ የአንዱ ከተማ የ27 እና 28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በኦቢኤን የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን እንደማያገኙ ታውቋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የምስል መብት ባለቤት የሆነው ኦቢኤን በሁለት ከተማ የሚደረጉ የሊጉን ጨዋታዎች ለአድማጭ ተመልካቾች እያደረሰ እንደሚገኝ ይታወቃል። ሊጉ አዲስ አበባ እና ሀዋሳ ላይ የተደረጉት የ25 እና 26ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን ዛሬ ያገባደደ ሲሆን የፊታችን ሰኞ የሚጀምረው የ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ የቴሌቪዥን ኩባንያው የአንዱን ከተማ ጨዋታዎች ብቻ በቀጥታ እንደሚያስተላልፍ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። በዚህም በሁለቱ ሳምንታት በአዲስ አበባ የሚደረጉ ጨዋታዎች ብቻ በኦቢኤን ሽፋን የሚያገኙ ይሆናል።
ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሰረት ኦቢኤን ሚያዚያ 10 አዲስ አበባ ላይ የሚደረገውን የግራንድ ፐሪክስ ኮንቲኔንታል ቱር ውድድር የስርጭት ስራ ስለሚሰራ የሀዋሳውን የሊጉን ውድድር ሽፋን የማይሰጥ ይሆናል።
ከቀጥታ ስርጭት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር እንደከዚህ ቀደሙ የቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት የማይኖራቸውን ጨዋታዎች በራሱ አማራጭ እንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል።

