ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ27ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ27ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች


የ27ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች !

ኢትዮጵያ መድን ከ ባሕር ዳር ከተማ

ከመጨረሻ 12 ጨዋታዎች 2 ጨዋታዎችን ብቻ አሽንፈው በ3 ተሸንፈው በ7 ጨዋታዎች የተሸነፉት ኢትዮጵያ መድኖች በዚህ የውጤት ማጣት ሂደት ከወራጅ ቀጠናው ጫፍ ላይ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል። በእንቅስቃሴ ረገድ ጠንካራ የሆነው ቡድኑ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ሲደርስ በተደራጀ የማጥቃት ቅንጅት ገብቶ ግቦችን ማስቆጠር አለመቻሉ ትልቁ ድክመቱ ነው። 29 ነጥቦችን ሰብስቦ 16ኛ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ ላለመውረድ በሚደረገው ትንቅንቅ ውስጥ ከገባበት አጣብቂኝ ለመውጣት በዛሬው ጨዋታ ማሸነፍን ብቻ እያለመ ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙት የጣና ሞገዶቹ በመጨረሻ 3 ጨዋታዎች ጊዮርጊስ እና አዳማን ሲያሸንፉ ከኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ ተጋርተዋል። በተሻለ የራስ መተማመን ላይ ከሚገኘው ቡድኑ ውስጥ ደግሞ ቁልፉ ተጫዋች አንተነህ ተፈራ ነው። አጥቂው ከላይ በተጠቀሱ ጨዋታዎች ቡድኑ ካስቆጠራቸው 4 ግቦች ሦስቱ በስሙ የተመዘገቡ ናቸው። በ35 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህርዳሮች ከወራጅ ቀጠናው ራቅ ብለው ለመደላደል የዛሬውን ድል አብዝተው እየፈለጉ ብርቱ ፍልሚያ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ባህር ዳር ከተማ ማንያዘዋል ካሳን በጉዳት ምክንያት አያገኝም።  በኢትዮጵያ መድን በኩል ዋንጫ ቱት በጉዳት ብሩክ በላቸው ደግሞ በቅጣት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 7 ጊዜ ተገናኝተው ባህር ዳር 3 ፣ መድን ሁለት ሲያሸንፉ በሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ባህር ዳር 10 መድን 9 ግቦችን አስቆጥረዋል።

 

ሀዋሳ ከተማ ከ ሽረ ምድረገነት

ከመጨረሻ 7 ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፉት ይባስ ብሎም ከመጨረሻ 3 ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ የሰበሰቡት ሐይቆቹ ቀስ በቀስ ከዋንጫ ፉክክሩ እየራቁ እየመጡ ነው። ከመሪው ሲዳማ ቡና በ10 ነጥቦች ርቆ 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ ወቅታዊ ብቃቱ ጥያቄን የሚያስነሳ ነው። በተለይም የቡድኑ መተማመኛ የነበረው ጠንካራው የመከላከል አደረጃጀት በእነዚሁ 3 ጨዋታዎች ብቻ 7 ግቦችን ማስተናገዱ ለውጤት ማጣታቸው እንደ ትልቅ ምክንያት ይጠቀሳል። የዛሬ ተጋጣሚያቸው ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ጥረት እያደረገ ያለ ቡድን እንደመሆኑም ቀላል ፈተና ላይጠብቃቸው ይችላል።

ከመጨረሻ 5 ጨዋታዎች 2 ነጥቦችን ብቻ የሰበሰቡት እና በወቅታዊ የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ የሚገኙት ሽረዎች ወሳኙ ሁለገብ ተጫዋቻቸው ሽመክት ጉግሳ ላይ የ6 ጨዋታዎች ቅጣት በመተላለፉ የሚያጡት ነገር ብዙ ነው። በተለይም በተጠቀሱት 5 ጨዋታዎች 2 ግቦች ብቻ ያስቆጠረውን የአጥቂ መስመር በራስ መተማመኑን በድጋሚ ለማምጣት የአንጋፋው ተጫዋች መኖር የሚያስፈልጋቸው ነበር። ቡድኑ በ28 ነጥቦች 18ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጡ ቶሎ ድሎችን ወደ ማሳካት መምጣት ይኖርበታል።

ሽረ ምድር ገነት በዛሬው ጨዋታ ሸመክት ጉግሳን በቅጣት ፤ መክበብ ደገፉ፣ ብሩክ ሐድሽ እና ፀጋይ ፀሐይን ደግሞ በጉዳት ምክንያት አያሰልፍም። በተጨማሪም ዋና አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐይ ሜዳ ላይ ተገኝተው ቡድናቸውን አይመሩም።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ ስድስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሀዋሳ 2 ጊዜ ፣ ሽረ 3 ጊዜ ሲያሸንፉ በቀሪው አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል። ምድረ ገነት ሽረዎች 11 ግቦችን ያስቆጠሩ ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው 12 ግቦችን ከመረብ አገናኝተዋል።

 

ድሬዳዋ ከተማ ከ መቻል

ከሁለት የሽንፈት እና ከአንድ የአቻ ውጤት በኋላ በመጨረሻው ሳምንት ሽረ ምድረገነትን 1-0 አሸንፈው ወደ ድል የተመለሱት ብርቱካናማዎቹ 32 ነጥቦችን ሰብስበው 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በውድድር ዓመቱ አንድም ጊዜ ተከታታይ ድል ያላሳካው ቡድኑ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ወደ 9ኛ ከፍ የሚያደርገው ሲሆን ከወራጅ ቀጠናው አካባቢ ለመራቅ ድሎች የሚያስፈልጉት ሲሆን በዛሬው ተጠባቂ ጨዋታም ያለ አሰልጣኙ ይታገሱ እንዳለ መሪነት በምን መንገድ ይቀርባሉ የሚለው የሚጠበቅ ነው።

ከሦስት ተከታታይ አቻዎች በኋላ የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ላይ የ3ለ1 ድል የተቀዳጁት መቻሎች  በዛ ጨዋታ ላይ የነበራቸው የማሸነፍ ፍላጎት እና ጠንካራ አቀራረብ ግሩም ነበር። አሁንም ቢሆን ከሊጉ መሪ ጋር የ11 ነጥቦች ርቀት ያለው ቡድኑ ከዋንጫ ፉክክሩ ላለመውጣት ማሸነፍ ብቸኛ አማራጩ ነው። ሆኖም በተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደው የድሬዳዋ መከላከል ፈታኝ ሊሆንባቸው ይችላል።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል አስቻለሙ ታመነ ከጉዳቱ ቢያገግምም የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። በሌላ ዜና የ6 ጨዋታዎች ቅጣት የተጣለባቸው አሰልጣኝ ይታገሱ በዛሬው ጨዋታ ቡድናቸውን ባይመሩም በቅጣቱ ዙሪያ ለአወዳዳሪው አካል ይግባኝ መጠየቃቸው ተሰምቷል። በመቻል በኩል ውብሸት ጭላሎ እና ቻላቸው መንበሩ በጉዳት እንዲሁም ዳዊት ማሞ በቅጣት ምክንያት አይኖሩም።

በሊጉ ከዚህ ቀደም ለ25 ጊዜያት የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች መቻሎች በአስራ ሁለት አጋጣሚ ማሸነፍ ሲችሉ በአንፃሩ ድሬዳዎች ደግሞ ሦስት ጨዋታዎች እንዲሁም የተቀሩት ዘጠኝ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።