ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ29ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ29ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

29ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራል፤ ጨዋታዎቹ የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል

ኢትዮጵያ መድን ከ ሀዋሳ ከተማ

በሰላሣ አንድ ነጥብ ወራጅ ቀጠናው ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ መድኖች ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ሐይቆቹን ይገጥማሉ። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ተከታታይ የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡት ኢትዮጵያ መድኖች ከገጠሟቸው ቡድኖች ጥንካሬ አንፃር ያስመዘገቡት ውጤት ለክፉ የሚሰጥ ባይሆንም ካሉበት አደገኛ ቀጠና ለመውጣት ግን ወደ ድል መመለስ ግድ ይላቸዋል። አጥቂው አማኑኤል ኤርቦ ግቦች ወደ ማስቆጠር መመለሱ ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ችግር ላለበት ቡድኑ ጥሩ ዜና ሲሆን በቀጣይም በሜዳ ላይ የሚያሳየው ጥሩ እንቅስቃሴ ወደ ውጤት ለመመንዘር አበክሮ መስራት ይጠበቅበታል።

በአርባ ሦስት ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀዋሳ ከተማዎች ከናፈቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። በሁለተኛው ዙር ባደረጓቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች አምስት አቻ፣ ሦስት ሽንፈት እና አንድ ድል ያስመዘገቡት ሐይቆቹ በሁለተኛው መንፈቅ በብዙ ረገድ ተዳክመዋል። ድል ካስመዘገበ አምስት የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠረው ቡድኑ የመጀመሪያውን ዙር ከመሪው ሲዳማ ቡና እኩል 35 ነጥብ በመሰብሰብ ቢያጠናቅቅም በቅርብ ሳምንታት ባስመዘገባቸው ውጤቶች በአሁኑ ወቅት ከመሪው በ11 ነጥብ ርቀት እንዲቀመጥ ሆኗል። ካለበት ውጤት መጥፋት ለመላቀቅም በቀዳሚነት ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት የተሳነውን የፊት መስመሩ ማሻሻል ይኖርበታል።

ሀዋሳ ከተማ ጌታነህ ከበደን ከቅጣት መልስ የሚያገኝ ይሆናል።

ሁለቱ ክለቦች በአጠቃላይ 32 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ 14 በማሸነፍ ከፍተኛ የበላይነት ሲኖረው መድን 6 ጊዜ አሸንፏል። 12 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። ሀዋሳ ከተማ 41 ፣ መድን 33 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ መቻል

አርባ ሁለት ነጥብ ሰብስበው 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የደረጃ መሻሻል ለማግኘት በሁለት ነጥብ ከፍ ብሎ ከተቀመጠው መቻል ጋር ይፋለማሉ።

በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ካደረጉ በኋላ ባከናወኗቸው አራት መርሐ ግብሮች ሁለት አቻ እንዲሁም አንድ አንድ ድልና ሽንፈት በእኩሌታ ያስመዘገቡት ኤሌክትሪኮች በቅርብ ሳምንታት የጣሏቸው ነጥቦች ወደ ሊጉ አናት ይበልጥ እንዳይጠጉ አድርጓቸዋል። ከመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ውስጥ በሁለቱ መሪነቱን ማስጠበቅ አቅቶት ነጥብ ለመጣል የተገደደው ቡድኑ በዛሬው ተጠባቂ ጨዋታ የተጠቀሰውን ድክመቱ ማረም እንዲሁም በሦስት መርሐ ግብሮች ስምንት ግባች ካስቆጠረ ወዲህ መጠነኛ መቀዛቀዝ የሚስተዋልበትን የፊት መስመሩ ማሻሻል ይኖርበታል።

ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በአስር ነጥብ ርቀት ላይ የሚገኙትና በአርባ አራት ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቻሎች በፉክክሩ ለመዝለቅ ከዛሬው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።

በኢትዮጵያ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ በወልዋሎ ከደረሰባቸው ሽንፈት መልስ ወደ ዛሬው ጨዋታ የሚቀርቡት መቻሎች በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ ላይ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ መጋራት ቢችሉም የቅርብ ሳምንታት እንቅስቃሴያቸውና የሊግ ውጤታቸው ቡድኑ እንደተሻሻለ ማሳያ ናቸው። ባለፉት ስምንት የሊግ መርሐ ግብሮች ሽንፈት ያልቀመሰው ቡድኑ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የማጠናቀቅ አባዜው ወቅታዊ ድክመቱ ሲሆን ለዚህ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ የአፈፃፀም ችግሩ ነው። ቡድኑ በርካታ ግቦች በማስቆጠር ከሊጉ ቀዳሚ ቢሆንም በፊት መስመሩ የሚስተወለው አባካኝነት እና ቀጣይነት የሌለው ብቃት ግን ከተጋጣሚው የተሻለ ብልጫ በወሰደባቸው ጨዋታዎች ጭምር ነጥብ እንዲጥል እያደረገው ይገኛል። በዛሬው ጨምሮ በቀጣይ መርሐ ግብሮችም የተጠቀሱትን ድክመቶች ማረም ይጠበቅበታል።

መቻል ውብሸት ጭላሎ እና ቻላቸው መንበሩን በጉዳት አለምብርሀን ይግዛውን ደግሞ በቅጣት ዛሬ አያገኝም። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ኢስማኤል ናሂማና እና ሀሰን ሁሴን በቅጣት ሄኖክ ገብረህይወት ደግሞ በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 31 ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ 11 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መቻል 5 አሸንፎ በ15 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። መቻል 32 ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ ደግሞ 44 ግቦች አሉት።


ሸገር ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

በሰላሣ አምስት ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት
ሸገር ከተማዎች በሰንጠረዡ አካፋይ ይበልጥ ለመደላደል የሚያስችላቸውን ነጥብ ለማግኘት ከጦና ንቦቹ ጋር ይፋለማሉ።

በመጨረሻው ሳምንት ባህርዳር ከተማን ሁለት ለባዶ በመርታት ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሱት ሸገር ከተማዎች በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ሁለት ተከታታይ ድሎች ለማግኘት ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። ጠንካራ ቡድኖች በገጠመባቸውና አምስት ነጥቦች በሰበሰበባቸው ያለፉትን ሦስት መርሐ ግብሮች ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በማሳየት ሽንፈት ያልቀመሰው ቡድኑ በቀዳሚነት በጥሩ የለውጥ ሂደት የሚገኘውን የማጥቃት አጨዋወቱ እድገት ማስቀጠል ይኖርበታል። በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ውስጥ አንድ ግብ ብቻ ካስተናገደው የተጋጣሚው የተከላካይ ክፍል የሚኖረው ፍልሚያም የጨዋታውን ውጤት ከሚወስኑ ነጥቦች አንዱ ነው።

በሰላሣ አራት ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች የማንሰራራት ጉዟቸውን ለማስቀጠል በአንድ ነጥብ እና አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ ከተቀመጠው ሸገር ከተማ ጋር ይጫወታሉ።

በፋሲል ከነማ ከደረሰባቸው የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ሽንፈት መልስ ሽረ ምድረ ገነትን አንድ ለባዶ በመርታት ደረጃቸውን ያሻሻሉበት ድል ያስመዘገቡት የጦና ንቦች የዛሬው ጨዋታ ከስጋት ቀጠናው ይበልጥ ለመራቅ በሚያድርጉት ጉዞ ያለው ወሳኝነት ትልቅ ነው። ወደ ራሱ የግብ ክልል የተጠጋ ጠጣር አቀራረብ እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር በሚጥረው ቡድን ውስጥ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ አስተናግዶ በአራቱ መረቡን አስከብሮ የወጣው የመከላከል አደረጃጀት ዋነኛ ጠንካራ ጎን ሲሆን በተጠቀሱት ጨዋታዎች ላይ ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የፊት መስመሩም መሻሻል የሚገባው ክፍል ነው። እስከ ሦስት ደረጃዎች ሊያሻሽሉ የሚችሉበትን ዕድል ለማመቻቸት በሚያደርጉት የዛሬ ጨዋታም የማጥቃት አጨዋወታቸውን ጥራት ከፍ ማድረግ ግድ ይላቸዋል።

በሸገር ከተማ በኩል ፍቅሩ አለማየሁ በአምስት ቢጫ ካርድ ምክንያት በቅጣት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ነው።

ቡድኖቹ በመጀመሪያው ዙር በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች 3 ለ 1 ማሸነፋቸው ይታወሳል።

አዳማ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

ስድስት ተከታታይ ሽንፈቶች ቀምሰው በውድድር ዓመቱ በመደዳ በርከት ያሉ ሽንፈቶችን በማስመዝገብ ቀዳሚ የሆኑት አዳማ ከተማዎች ከሰሞነኛው መጥፎ ውጤት ለመውጣት ብርቱካናማዎቹን ይገጥማሉ። በሰላሣ ሦስት ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ ከቅርብ ሳምንታት ባስመዘገባቸው በርካታ ሽንፈቶች ከወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥብ ርቀት ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል። በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ ዘጠኝ ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው ሀያ ሰባት ነጥብ ሀያ ሁለቱን ጥሎ አምስቱን ብቻ ያሳካው ቡድኑ ከናፈቀው ድል ጋር ለመታረቅ ዘርፈ ብዙ ለውጦች ማድረግ ግድ ይለዋል። በተለይም የግብ ዕድሎችን እየፈጠረ የማይገኘው የማጥቃት አቀራረባቸው ስር ነቀል ለውጥ የሚፈልግ የቡድኑ ዋነኛ ችግር ነው።

ሰላሣ ሁለት ነጥብ ሰብስበው 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ከወራጅ ቀጠናው አፋፍ ሊያርቃቸው የሚችል ድል ለማግኘት በቀጠናው ቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኘው አዳማ ከተማ ይፋለማሉ።

በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በመቻል እና ሲዳማ ቡና ሽንፈት ያስተናገዱት ብርቱካናማዎቹ በሁለተኛው ዙር በብዙ ረገድ ተዳክመዋል። በመጀመሪያው ዙር በአስራ ዘጠኝ የጨዋታ ሳምንታት አምስት ሽንፈቶችን ብቻ ያስመዘገበው ቡድኑ በሁለተኛው መንፈቅ በተደረጉ ዘጠኝ ጨዋታዎች ውስጥ በአምስቱ ሽንፈት ማስተናገዱም የዚህ ማሳያ ሲሆን በቅርብ ሳምንታት ባስመዘገባቸው ውጤቶችም ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ርቀት እንዲቀመጥ ሆኗል። ከተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም ከሚያልመው አዳማ ከተማ ጋር በሚያደርጉት የዛሬ ጨዋታ የተከላካይ ክፍላቸው ከባድ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ባይጠበቅም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦችን ያስተናገደው እና በሁለተኛው ዙር በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ መረቡን አስከብሮ የወጣው የተከላካይ መስመራቸው መሻሻል የሚገባው ክፍል ነው።

ድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኙ ይታገሱ እንዳለ እና ተከላካዩ ሬድዋን ሸረፋን በቅጣት አያገኝም።

ሁለቱ ቡድኖች በአጠቃላይ በሊጉ 27 ጊዜ ሲገናኙ አዳማ ከተማዎች 12 ጊዜ ባለድል በመሆን የበላይ ሲሆኑ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ በ7 ይከተላሉ የተቀሩት 8 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተቋጩ ነበሩ። በጨዋታዎቹ አዳማዎች 31 ሲያስቆጥሩ ድሬዎች በአንጻሩ 25 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።