መድኖች ከመመራት ተነስተው ሐይቆቹ 2ለ1 በማሸነፍ ከአራት ድል አልባ ሳምንታት በኋላ ደረጃቸውን ያሻሻሉበትን ድል ሲያገኙ ሸገር ከተማ እና ወላይታ ድቻ 0ለ0 ተለያይተዋል።
ኢትዮጵያ መድን ከሀዋሳ ከተማ
የ29ኛ ሳምንት ቀዳሚው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድንን ከሀዋሳ ከተማ ቀን ሰባት ሰዓት ሲል አገናኝቷል። የጨዋታ ጅማሮ ላይ የተሻሉ የነበሩት ሐይቆቹ 7ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ የሆኑበት ግብ አስቆጥረዋል። ሽመልስ በቀለ ከማዕዘን ምት ያሻገረው ኳስ ተባረክ ሄፋሞ በግንባሩ ገጭቶ መሪ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ግብ ካስተናገዱ በኋላ የተነቃቁት መድኖች አማኑኤል ኤርቦ ሙከራ አድርጎ ዳግም ተፈራ እንደምንም ከመለሰበት በኋላ ብዙም ሳይቆይ የአቻነት ግብ አግኝተዋል። በግራ መስመር በኩል በተደጋጋሚ ኳስ ሲያሻግር የነበረው አልፍሬድ ኩሩንዚዛ ያሻገረውን ኳስ አማኑኤል ኤርቦ ሾልኮ በመውጣት መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።

ፈጣን የመድንን የማጥቃት እንቅስቃሴ እያስመለከተን በቀጠለው በጨዋታው ቤንጃሚን ኮቴ በግንባሩ ገጭቶ ግብ ጠባቂው የተቆጣጠረበት እንዲሁም አማኑኤል ኤርቦ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ጠንከር ያለ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው ያገደባቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። ደቂቃዎቹ በሄዱ ቁጥሩ ቡድኖቹ እየተቀዛቀዙ የመጡበት ጨዋታው በአንፃራዊነት በመድን የበላይነት አጋማሹ ተገባዷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ ሦስት ተጫዋች ቀይረው የተመለሱት ሐይቆቹ ግብ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። ያሬድ ብሩክ 73ኛው ደቂቃ ላይ ጠንካራ ሙከራ አድርጎ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቶባቸዋል። በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ የነበሩት መድኖች መሪነቱን መረከብ የቻሉበት ግብ 79ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥረዋል። የቆመ ኳስ በፍጥነት ያሬድ ካሳዬ እና ወገኔ ገዛኸኝ ተቀባብለው ወደ ሳጥን ሲያሻሙ ሳጥን ውስጥ የነበረው አማነኤል ኤርቦ በግንባሩ በማስቆጠር መሪ አድርጓቸዋል። ሐይቆቹ በጨዋታው ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ተጭነው እየተጫወቱ በጌታነህ ከበደ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ካደረጉት ሙከራ ባሻገር ሌላ አጋጣሚ ሳይፈጥሩ ጨዋታው በመድን 2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ሸገር ከተማ ከወላይታ ድቻ
በአዲስ አበባ ስታዲየም የእለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሸገር ከተማን ከወላይታ ድቻ ያገናኘ ሲሆን ቡድኖቹ በመጀመሪያ አጋማሽ ቀዳሚ ለመሆን በተደጋጋሚ ከሳጥን ሳጥን እየደረሱ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አድርገዋል። አደገኛ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ሸገሮች 8ኛው ደቂቃ ላይ ካሌብ በየነ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ምስጋናው ሚልክያስ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው በተቆጣጠረበት ሙከራ ጀምረዋል። ከእነዚህ ሙከራዎች ባሻገር 33ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ደቂቃ በኋላ በቆመ ኳስ ቡልቻ ሹራ ሙከራ አድርጎት የግቡ አግዳሚ የመለሰባቸው፤ 38ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም ፍቅሬ ከርቀት አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ያገደበት ሌላኛው በአጋማሹ ተጠቃሽ የሸገሮች ሙከራዎች ነበሩ።

ልክ እንደተጋጣሚያቸው ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉት የጦና ንቦች ቴዎድሮስ ታፈሰ ያሻገረውን ኳስ ካርሎስ ዳምጣው ሳጥን ውስጥ አግኝቶ ባህሩ ነጋሽ በጥሩ ቅልጥፍና የሸፈነበት እና ሳሊፉ ኢብራሂም ከሳጥን ውጪ አድርጎ ለጥቂት ከግቡ ርቆ ባለፈባቸው ሙከራዎች መሪ ለመሆን የቀረቡ አደገኛ አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል። እንዲሁም የአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ ካርሎስ ዳምጠው በቆመ ኳስ ያደረገው አደገኛ ሙከራ በግብ ጠባቂው ታግዶበት ግብ ባይቆጠርበትም አደገኛ እና አስቆጪ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ያስመለከተን ሳቢው የመጀመሪያ አጋማሽ ተገባዶ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ጨዋታው ቀጥሎ ቡድኖቹ በጥሩ መነሳሳት ሶስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ወደፊት እየሄዱ ጥረት ማድረግ የቻሉ ቢሆንም ጥረታቸው ፍሬ ማፍራት ሳይችል ቀርቷል። ሸገር ከተማ አንፃራዊ ብልጫ የወሰደባት ጨዋታውም ግብ ሳያስተናግድ ነጥብ በማጋርት ተጠናቋል።

