ሪፖርት| መቻል ወሳኝ ድል ሲያሳካ አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት| መቻል ወሳኝ ድል ሲያሳካ አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

መቻሎች ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማሸነፍ ከመሪው ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ሲያጠቡ አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ መቻል

ጨዋታው ገና በጅማሮው በኤሌክትሪክ በኩል በበረቱ ጥቃቶች የታጀበ ነበር። በ1ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ ገብረማርያም ከርቀት የሞከራትን እና አቤል ሀብታሙ በግንባር የገጨውን ኳስ የግቡ ዘብ ኦሊዮንዜ ናፍያን በድንቅ ቅልጥፍና አድኖባቸዋል። መቻሎችም 8ኛው ደቂቃ ላይ በበረከት ደስታ አማካኝነት አደገኛ ሙከራ ቢያደርጉም ከመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች በኋላ የሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት ፍጥነት እየቀነሰ በመምጣቱ የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በኳስ ቁጥጥር እና በማጥቃት ረገድ የተሻለ እንቅስቃሴ አሳይተዋል። በ56ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ወልደዮሐንስ ከቅጣት ምት የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት በአግዳሚው የተመለሰበት አጋጣሚ ለኤሌክትሪክ እጅግ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።

ሆኖም ኤሌክትሪኮች ወደ ፊት ገፍተው በሚያጠቁበት ወቅት የተፈጠረውን ክፍተት የተጠቀሙት መቻሎች በ61ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል። በረከት ደስታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ኮሊንስ ኮፊ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት በመቀየር መቻልን መሪ አድርጓል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ጨዋታው መቀዝቀዝ የታየበት ሲሆን ተጨማሪ ሙከራዎች ሳይመዘገቡ መቻል ባለሦስት ነጥብ መሆን ችሏል።

አዳማ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ባገናኘው የምሽቱ መርሃ-ግብር አዳማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በመናፍ አወል እና ሚካኤል ሳፉ አማካኝነት ተከታታይ የግብ እድሎችን ቢፈጥሩም የግቡ አግዳሚ ሙከራዎቻቸውን መልሶባቸዋል።

አዳማ ከተማዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። በ31ኛው ደቂቃ ላይ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በመነሳት በግራ መስመር የፈጠሩትን ጥቃት ቢኒያም አይተን አመቻችቶ ሲያቀብል አቡበከር ሳኒ በጥሩ አጨራረስ ኳስ እና መረብን አገናኝቶ ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ድሬዳዋ ከተማዎች ከዕረፍት መልስ የተጫዋች ለውጦችን በማድረግ ከፍተኛ ጫና ፈጥረዋል። በያሬድ ታደሰ አማካኝነት የግቡ አግዳሚ የመለሰባቸውን ድንቅ ሙከራ ካደረጉ በኋላ በ79ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው አብዱልሰላም የሱፍ ከያሬድ ታደሰ የፈረሰውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩ ድሬዳዋዎች የድል ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። አቤል ነጋሽ መትቶት ግብ ጠባቂውን ያለፈውን ኳስ ተከላካዩ ሚካኤል ሳፉ ከመስመር ላይ በማውጣት አዳማን ከሽንፈት ሲታደግ ጨዋታውም 1-1 በሆነ ውጤት ፍጻሜውን አግኝቷል።