በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና 0 ለ 0 ተለያይተዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ የወሰዱበትና በግብ ቀዳሚ ለመሆን የተንቀሳቀሱበት ነበር።
በሲዳማ ቡና በኩል ያሬድ ባየህ ከቆመ ኳስ የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ያደረገውና በግብ ጠባቂው የተመለሰው የግብ አጋጣሚ ፤ ደስታ ደሙ ከማዕዘን ተሻምታ ሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ ያገኛትን ኳስ መቶ ወደ ውጭ የወጣችበት ሙከራ እንዲሁም ብርሃኑ በቀለ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ደግፌ አለሙ ያሻማትን ኳስ ከሳጥን ውስጥ መሬት ለመሬት መቶ በግቡ ቋሚ ለጥቂት የወጣችው አጋጣሚ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ።
ጨዋታውን በጥሩ የማጥቃት መንፈስ የጀመሩት
ፈረሰኞቹም ሀብታሙ ጉልላት አሻግሯት ፍፁም ጥላሁን በግንባሩ ገጭቶ ባደረጋት ሙከራ እና አዲሱ አቱላ ከመዓዝን ተሻምታ ሳጥን ውስጥ ብቻውን ሆኖ በችኮላ ባልተጠቀመባት አጋጣሚ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ ጥሩ ፉክክር ያስመለከተን የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለጊዜም ግብ ሳይቆጠርበት ተቋጭቷል።

ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ሲዳማ ቡናዎች ጫና የፈጠሩበት እንዲሁም የፈረሰኞቹ የተሻለ የመከላከል ጥንካሬ የታየበት ነበር።
በአጋማሹ ሀብታሙ ጉልላት ከቆመ ኳስ ሞክሮት ግብ ጠባቂው የተቆጣጠረው ኳስ በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ባደረጉት ፈረሰኞቹ በኩል የተደረገ ብቸኛ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲሆን የተሻለ ብልጫ በነበራቸው ሲዳማ ቡናዎች በኩል ደግሞ ፍቅረኢየሱስ ተወልደ ብርሃን ከሳጥን ውጪ ሆኖ ያደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ እና ፍቅረኢየሱስ ተወልደ ብርሃን አሻምቷት ብሌሥ ናጎ በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ መቷት ከፍ ብላ የወጣችው ኳስ ይጠቀሳሉ። ጥሩ ፉክክር የተደረገበትና ለተመልካች ሳቢ የነበረው ጨዋታም ግብ ሳይቆጠርበት ነጥብ በመጋራት ተጠናቋል።

