መሪው ሲዳማ ቡና ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ ሽንፈት ሲያስተናግድ ወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለግብ ተለያይተዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሲዳማ ቡና
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 32ኛ ሳምንት መክፈቻ በነበረው በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ሄኖክ አርፌጮ እና ኢዮብ አለማየሁ ከቅጣት ምት በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ አቤል ያለው እና ዮሴፍ ዮሐንስ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ግልጽ የግብ ዕድሎች ሳይፈጠሩና ግብ ሳያስቆጥሩ ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ሲዳማ ቡናዎች በመስፈን ታፈሰ አማካኝነት ለግብ የቀረበ ሙከራ በማድረግ ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም ግቡን ግን ሀዲያ ሆሳዕናዎች ቀዳሚ ሆነው አግኝተዋል። በ62ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ተከላካዮች በቅጡ ያላራቁትን ኳስ ደስታ ዋሚሾ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታትና በግብ ጠባቂው ስህተት ታክሎበት የቡድኑን መሪነት አብስሯል።

ጨዋታውም ተጨማሪ የግብ ሙከራዎችን ሳያስመለክተን በሀዲያ ሆሳዕና 1 ለ 0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቡድኑ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን በማስመዝገብ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል። በአንጻሩ ሲዳማ ቡናዎች የገጠማቸው ሦስተኛ ተከታታይ ሽንፈት ለዋንጫ ሲያደርጉት የነበረውን ግስጋሴ ወደ አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ ውጤት ሆኖባቸዋል።
ወላይታ ድቻ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በበርካታ የሁለቱም ቡድኖች ደጋፊዎች ታጅቦ በጀመረው የሁለቱ ክለቦች ፍልሚያ በመጀመሪያው አጋማሽ ተቀራራቢ የሚባል የኳስ ቁጥጥር የታየበት ነበር። ይሁን እንጂ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል በመድረስ ረገድ ወላይታ ድቻዎች የተሻሉ የነበሩ ሲሆን በተለይም በ16ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ኃይለማርያም አክርሮ መትቶ የግቡን ቋሚ ታክኮ የወጣበት ኳስ በአጋማሹ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርጎታል።

ከእረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኳስ ቅብብልና የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ራሳቸውን አሻሽለው የቀረቡበት ነበር። ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረስ ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ግን ጥራት ያላቸውን የግብ ዕድሎች ወደ ሙከራ መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ሁለቱም ቡድኖች ጨዋታውን ለማሸነፍ ያደረጓቸው ጥረቶች ሳይሳኩ ቀርተው የ90 ደቂቃው ትንቅንቅ ያለምንም ግብ ዜሮ ለዜሮ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። በዚህም ክለቦቹ ነጥብ ተጋርተው ሜዳውን ለቀዋል።

