ሪፖርት | ወልዋሎ ዓ/ዩ እና ሸገር ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል

ሪፖርት | ወልዋሎ ዓ/ዩ እና ሸገር ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል

በቀጣዩ የውድድር ዘመን በሊጉ የመቆየታቸውን ተስፋ ለማለምለም ሁለቱ ክለቦች ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ ዜሮ ለዜሮ በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል::

ለቀጣዩ የውድድር ዘመን በሊጉ ለመቆየት ብርቱ ትግል እያደረጉ የሚገኙ ክለቦችን ባገናኘው በዚህ ወሳኝ ፍልሚያ በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ወገኖች በኩል ተመጣጣኝ የኳስ ፍሰትና እንቅስቃሴ ተስተውሏል። ይሁን እንጂ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስና ቀጥተኛ የግብ አደጋዎችን በመፍጠር ረገድ ቢጫ ለባሾቹ የተሻሉ ነበሩ። በዚህም በ15ኛው ደቂቃ ላይ ኮንኮኒ ኻፊዝ በግንባሩ ገጭቶ የሞከረውን እንዲሁም በ35ኛው ደቂቃ ላይ ሰመረ ሀፍታይ ከግብ ጠባቂ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ያገኘውን ወርቃማ ዕድል የሸገር ከተማው ግብ ጠባቂ ምንተስኖት የግሌ ባሳየው ድንቅ ቅልጥፍና እና አስደናቂ ብቃት ግብ ከመሆን ታድጎባቸዋል። ከእነዚህ ተጠቃሽ ሙከራዎች ውጪ ተጨማሪ ግብ ሳይመዘገብ የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ምንም ግብ በባዶ መጠናቀቅ ችሏል።

ከእረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች በጨዋታው የድል ነጥብ ለማስመዝገብ ይረዳሉ ያሏቸውን  ተጫዋቾችን ቀይረው ወደ ሜዳ በማስገባት ጥረታቸውን አጠናክረዋል። ይሁን እንጂ በሊጉ ለመቆየት የሚደረገው ፍልሚያ የፈጠረው ጫና ሳቢያ ሁለቱም ወገኖች ከተጋጣሚ ጥቃት ራስን የመጠበቅ ጥንቃቄን ቀዳሚ ምርጫቸው አድርገዋል። ወደፊት ከመግፋት ይልቅ የኋላ መስመራቸውን አጥብቀው በሚፈግፈግ መጫወትን መምረጣቸውም ጨዋታው ሚዛናዊ ግን ደግሞ ጥጥቅ ያለ የታክቲክ ፍልሚያ ብቻ ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎታል። በዚህም ምክንያት በሁለተኛው አጋማሽ የደጋፊን ቀልብ ሊስብና ግብ ሊሆን የሚችል ይሄ ነው የሚባል የጎላ ሙከራ ሳናይ ጨዋታው ያለ ምንም ግብ 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት ፍጻሜውን አግኝቷል።