ሐይቆቹ ሁለተኛ ተከታታይ ድል ተቀዳጁ

ሐይቆቹ ሁለተኛ ተከታታይ ድል ተቀዳጁ

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ4ኛው ሳምንት የምድብ አንድ የሁለተኛ ቀን ብቸኛ ጨዋታ ላይ ሀዋሳ ከተማ ተከታታይ ድሉን ሲያስመዘግብ መቐለ 70 እንደርታ ሁለተኛ ተከታታይ ሽንፈት አስተናግዷል።

የዕለቱ ብቸኛ የምድብ አንድ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ መቐለ 70 እንደርታዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር በመያዝ ሐይቆቹ ደግሞ በቀጥተኛ አጨዋወቶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት ነበር። በ7ኛው ደቂቃ ላይም ያሬድ ብሩክ በረዥሙ የተሻገረችለትን ኳስ መቶ ሶፎንያስ ሰይፈ ከመለሰው በኋላ ጌታነህ ከበደ የተመለሰውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ሐይቆቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ በኋላ የተሻለ ብልጫ የነበራቸው መቐለ 70 እንደርታዎችም በ24ኛው ደቂቃ ላይ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ሱሌይማን ሐሚድ ከቅጣት ምት በቀጥታ ባስቆጠራት ግብ አቻ መሆን ችለዋል። በአጋማሹ በምዓም አናብስት በኪቲካ ጅማ እንዲሁም በፍፁም አለሙ አማካኝነት ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ሁለቱም ሙከራዎች በሰዒድ ሀብታሙ መክነዋል። በሐይቆቹ በኩል ደግሞ በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃ አብነት ደምሴ ያደረጋት ሙከራ ትጠቀሳለች።

በጥፋቶች እንዲሁም በተደጋጋሚ የተጫዋቾች ጉዳትና የህክምና እርዳታዎች እየተቆራረጠ የተካሄደው ሁለተኛው አጋማሽ ሳቢ እንቅስቃሴ ያልተደረገበት ነበር። በ46 ኛው ደቂቃም
ቢኒያም በላይ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል አሻግሯት ያሬድ ብሩክ በጥሩ አጨራረስ ባስቆጠራት ግብ ሐይቆቹ መሪ መሆን ችለዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ምዓም አናብስት በሁለት አጋጣሚዎች በሱሌይማን ሐሚድ  እንዲሁም በፍፁም አለሙ አማካኝነት ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር የቻሉት ግን ሐይቆቹ ነበሩ፤ በ89ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከቆመ ኳስ ያስቆጠራት ግብም የሀዋሳ ከተማን መሪነት ከፍ ማድረግ ችላለች።

በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች መቐለ 70 እንደርታዎች ጫና ፈጥረው ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም በ83ኛው ደቂቃ የመቐለ 70 እንደርታው ፍሬዘር ካሳ መደበኛ ሰዓት ተጠናቆ በተሰጡት ጭማሪ ደቂቃዎች ደግሞ የሀዋሳ ከተማው በረከት ሳሙኤል በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጡበት ተደጋጋሚ ጥፋቶች የተስተዋሉበት ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።