👉 “የተሰማኝ ስሜት በቃላት የሚገለፅ አይደለም።” ከነዓን ማርክነህ

👉 “የተሰማኝ ስሜት በቃላት የሚገለፅ አይደለም።” ከነዓን ማርክነህ

👉 “የተሰማኝ ስሜት በቃላት የሚገለፅ አይደለም።”

👉 “ዓላማ እስካለህ ድረስ እነዚህ ነገሮች በጣም ቀላል ናቸው።”

👉 “ከሀገርህ ውጭ ወጥተህ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ መጨረስ በጣም ደስ ይላል።”

👉 “ሶከር ኢትዮጵያ ለሀገራችን ተጫዋቾች እያደረጋችሁ ያላችሁት ነገር በጣም ደስ ይላል።”

በኦማን ሊግ መድመቅ የቻለው ከነዓን ማርክነህ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እነሆ !

ለኦማኑ አል ሸባብ  እየተጫወተ እና ድንቅ ወቅታዊ ብቃት እያሳየ የሚገኘው ኢትዮጵያዊው ከነዓን ማርክነህ ባሳለፍነው ሳምንት ሀትሪክ በመስራት የጎል መጠኑን በ21 በማድረስ የኦማን ጂንዳል ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሲሆን ቡድኑ በአህጉራዊው ኤስያ ቻሌንጅ ሊግ ባደረገው ጉዞ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። በዚህ መነሻነት ከነዓን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንዲህ አሰናድተነዋል።

የኦማን ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ስለመሆኑ ?

“በጣም ነው የማመሰግነው። በመጀመሪያ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ እኔ ጋር ስለመጣችሁ አመሰግናለሁ። ሶከር ይታወቃል ቃለመጠይቆችን በማድረግ እና ለሀገራችን እግር ኳስ እና ለሀገራችን ተጫዋቾች እያረጋችሁ ያለው ነገር በጣም ደስ ይላል፤ ይሄንን ነገር ቀጥሉ ማለት ፈልጋለሁ። በመቀጠል የተሰማኝ ስሜት በቃላት የሚገለጽ አይደለም። ከሀገር ውጪ ወጥተህ የጎል አግቢነት ክብረወሰን ተጋርተህ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ መጨረስ በጣም ደስ ይላል፤ እንደዚያውም ከኋላው በጣም ብዙ ልፋት አለው፤ በዚህ አጋጣሚ የልፋቴን ወጤት ስላገኘሁ በጣም ነው ደስ ያለኝ።”

ዓመቱ ለአንተ እንዴት አለፈ?

“የዘንድሮው ጉዞ እንደዚህ እንደምናገረው ቀላል አልነበረም ፤ ከኋላ ብዙ ነገር አለ። በጣም ብዙ ተለፍቶበታል፤ እንደዚህ ዓይነት ውጤት ዝም ብሎ አይመጣም። ከባድ ጉዞ ነበር ግን በድል ጨርሼዋለሁ እግዚአብሔር ይመስገን።”

በቀጣይ ምን ታስባለህ ?

“በመቀጠል የማስበው አሁን እያረኩት ካለው በላይ አቅሜ እስከፈቀው ድረስ መሄድ ነው የምፈልገው። በየሄድኩበት ቦታ ከፍተኛ ግቢ አስቆጣሪ፣ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሆኜ መጨረስ ነው የምፈልገው ለዛ አሁን ያለውን ነገር ማስቀጠል ነው ፍላጎቴ።”

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሁን ባለው ሁኔታ ከፍተኛ ክፍያ ስላለ ተጫዋቾች ወደ ውጭ ወጥተው ለመጫወት ያላቸው ፍላጎት አናሳ ነው። ብዙ ጥረት አያደርጉም። በዚህ ጉዳይ ለተጫዋቾች ምን ዓይነት መልዕክት አለህ? ምን ማወቅ አለባቸው ትላለህ?

“እውነት ለመናገር እኛ ሀገር ያለው የገንዘብ ክፍያ ትልቅ ነው የሚባለው ነገር ውጭ ካለው ነገር አንፃር በጣም ትንሽ ነው። ክፍያው በጣም ብዙም አይደለም። ግን ደግሞ በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ካያችሁት ብዙ ሊሆን ይችላል። ከውጭው አንፃር ከታየ ግን በጣም ትንሽ ነው።

የተመቸ ቦታ ካለመልቀቅ ጋር ይያያዛል። ይህ ማለት ሀገር ውስጥ ነው ያለኸው፣ በምታቀው አካባቢ፣ ቋንቋ፣ ባህል ነው። ይህ ደግሞ የተመቸ ቦታ ስለሚባል ይሄንን ላለመልቀቅ ከመፈለግ ይመስለኛል። ከሀገር ወጥተህ  በምትጫወትበት ሰዓት አዲስ አካበቢ ፣ ባህል ብዙ ነገሮች አዲስ ነው የሚሆኑት ግን ይህንን ጊዜ ካለፉት በኋላ ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት የሚመለሰው።”

የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ከሀገር ሲወጡ አይሳካላቸውም ይባላል ወይም ቶሎ ይመለሳሉ ይባላል። አንተ ያንን ፈተና እንዴት አልፈኸው ነው በአንድ ዓመት ውስጥ ይህንን ትልቅ ስኬት ያሳካኸው?

“ይሄ ወሬ ነው ብዬ አስባለሁ። ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ሆኜ በሄድኩባቸው ሁሉ ውጤታማ ሆኜ ነው እየወጣው ያለሁት። እኔ እንደማስበው ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ሲወጡ ለእግርኳሱ የሚያስፈልገው ነገር የምታደርግ ከሆነ ለምን የማይሳካልህ ይሆናል? አንድ አንዴ እግር ኳሳዊ በሆነ መንገድ ከአሰልጣኝ ጋር ላትስማማ ትችላለህ ወይ የጨዋታው ሲስተም ላይመችህ ይችላል። ከዛ ውጭ ባለው ነገር የምትሰራ ከሆነ እግር ኳሱ የሚፈልገውን ነገር የምታደርግ ከሆነ ምንድን ነው ወጥተህ የማይሳካልህ? ስለዚህ እግርኳሱ የሚፈልገውን ካደረክ የማይሳካበት ምንም ምክንያት የለም።”

በአዲስ ሀገር በአዲስ ባህል በአዲስ ሊግ ወዲያውኑ ውጤታማ መሆን በጣም ከባድ ነው። ላንተ ስኬት ያገዘህ ዋነኛ ነገር ምንድን ነው? አየሩን ምግቡን አኗኗራቸውን እንዴት በዚህ ፍጥነት ልትለምደው ቻልክ?

“በፍጥነት ልለምድ የቻልኩበት ምክንያት አላማ እስካለህ ድረስ እነዚህ ነገሮች በጣም ቀላል ናቸው። ዋናው የሄድክበት ዓላማ ነው የሚወስነው። ለዛ ነው ብዙም በእንደነዚህ ያሉ ነገሮች ያልተቸገርኩት።”