ሆሳእና ከነማ ወሳኝ ተጫዋቾችን በማቆየት የቀጣይ የውድድር ዘመኑ ለመጀመር ተዘጋጅቷል፡፡ ቡድኑ ውላቸውን በማደስ በክለባቸው ያቆዪዋቸው ተጫዋችች ዱላ ሙላቱ ፣ ሐብቴ ከድር ፣ ኄኖክ አርፊጮ ፣ አየለ ተስፋዬ ፣ ተዘራ አቡቴ ፣ ውብሸት አለማየሁ ፣ ንጋቱ ዱሬ ፣ ታረቀኝ ጥበቡ ፣ ሃብቶም ገ/እግዚአብሄር እና አበባው ታምሩ ናቸው፡፡
ቡድኑ እስካሁን ሙሉ ለሙሉ የተረጋገጠ አዲስ ተጫዋች ያላስፈረመ ሲሆን እንደ ክለቡ አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ገለፃ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣት ተጫዋቾችን ለማስፈረም እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡
‹‹ እግርኳስን የጠገበና የመጫወት ፍላጎቱ የቀነሰ ተጫዋች አላስፈርምም፡፡ የመጫወት ፍላጎትና የማደግ ጉጉት ያለው ተጫዋች እንጂ በትልልቅ ክለቦች ወንበር ሲያሞቅ የቆየ ተጫዋች አላስፈርምም፡፡ ትልቁ ነገር በርካታ ተጫዋቾች በክለቡ እንዲቆዩ ማድረጋችን ነው፡፡ በቡድናችን ቆይታቸውን ያላረጋገጡ 14 ተጫዋቾች የሚገኙ ሲሆን በማመጣቸው አዳዲስ ተጫዋቾች መሰረት የሚቀነሱ ተጫዋቾች ይኖራሉ፡፡ የቋሚነት እድል ያላገኙና በአመቱ ብዙም ግልጋሎት ያልሰጡኝን እቀንሳለሁ፡፡ ››
‹‹ ከሲዳማ ቡና ፣ ሃዋሳ ከነማ አዳዲስ ተጫዋቾች ለማስፈረም እንቅስቃሴ እያደረግን ሲሆን በቀናት ውስጥ እናስፈርማለን ብለን እንጠብቃለን፡፡ ተጫዋቾቹ ወጣት እና ተስፋ የሚጣልባቸው ናቸው›› ብለዋል፡፡
ቡድኑ ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንዲያድግ ከፍተኛውን ሚና ከተጫወቱት ተጫዋቾች መካከል የሚጠቀሰው ቴዎድሮስ መንገሻ ከክለቡ ጋር መለያየቱ እውን የሆነ ቢሆንም ክለቡ ግን ተጫዋቹን በከፍተኛ ገንዘብ ለመመለስ እየተደራደረ መሆኑን አሰልጣኙ ተናግረዋል፡፡
‹‹ የቴድሮስ መንገሻ ጉዳይ አሳስቦኛል፡፡ ወላይታ ድቻ በብሄራዊ ሊጉ የመጀመርያ ጨዋታዎች ያሳውን አቋም ተመልክቶ አስፈርሞታል፡፡ ባለን መረጃ መሰረት የፈረመው በክልሉ ፌዴሬሽን በመሆኑ የተሸለ ክፍያ ከፍለን በድርድር ለማስመለስ ጥረት እያደረግኩ ነው፡፡ ›› ሲሉ ስለ ቴዎድሮስ መንገሻ ወቅታዊ ሁኔታ አስረድተዋል፡፡
ሆሳእና ከነማ ከአድካሚው የብሄራዊ ሊግ ውድድር በኋላ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በአዲሱ አመት የመጀመርያ ቀናት በሆሳእና ከተማ እንደሚመርም አሰልጣኝ ግርማ ጠቁሟል፡፡
‹‹ ከመስከረም 2-4 ባለው ጊዜ ውስጥ ዝግጅት እንጀምራለን፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ ለመፎካከር ጠንካራ ዝግጅት እናደርጋለን፡፡ በመጣበትአመት ወደ ከፍተኛ ሊግ የተመለሰው የወልድያ የውድድር ዘመን ብዙ ትምህርት ሰጥቶናል፡፡ ቡድ በመጣበት አመት እንዳይወርድ ከፍተኛ ስራ የምሰራበት ወቅት ላይ ደርሻለሁ፡፡ ›› ሲሉ አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡
ከክለቡ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና ሆሳዕና ከነማ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በማለፉ ከክልሉ መንግስት እና ከተማ መስተዳድሩ ከፍተኛ ሽልማት ይጠብቀዋል፡፡ ቡድኑ ፕሪሚየር ሊጉን መቀላቀሉን ባረጋገጠበት ወቅት ቃል የተገባላቸው ከ200 ሺህ እስከ 300ሺህ ብር የሚገመት ገንዘብ ባበረከቱት አስተዋፅኦ ልክ እንደሚሸለሙ ተነግሯል፡፡ የክልሉ መንግስትም ለክለቡ ዘመናዊ አውቶብስ በስጦታ እንደሚያበረክት ይጠበቃል፡፡ የክልሉ መንግስት ከዚህ ቀደም ሲዳማ ቡና ፣ አርባምንጭ ከነማ እና ወላይታ ድቻ ወደ ትልቁ ሊግ ሲያድጉ የተጫዋቾች መጓጓዣ አውቶብስ ማበርከቱ የሚታወስ ነው፡፡