የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ሦስተኛ የጨዋታ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር በአዳማ ከተማ እየተካሄድ ሲገኝ በዛሬ የ3ኛ ቀን ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማ ፣ ወላይታ ድቻ እና መከላከያ ማሸነፍ ችለዋል።

03:00 ላይ የመጀመርያው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን ከአፍሮ ፅዮን ሲያገናኝ ሀዋሳ በተስፋኛ አጥቂዎቹ የግል ብቃት ታግዞ 3-0 አሸንፎ ወጥቷል። አዝናኝ እግርኳስን ከተመጣጣኝ ፉክክር ጋር መመልከት በቻልንበት የመጀመርያው አጋማሽ የሁለቱም ቡድኖች ጨዋታ በጎል ሙከራ ረገድ የተመከትነው ግን ጥቂት ነበር ። ሀዋሳዎች ወደ ፊት በመሄድ ተጭነው ቢጫወቱም የአፍሮ ፅዮን ተከላካዮችን አልፈው ጎል ለማስቆጠር በመቸገራቸው አጥቂዎቻቸው በቀጥታ ከሳጥን ውጭ የጎል እድል ለመፍጠር ተገደዋል። ለዚህም ማሳያው የሀዋሳው መስፍን ታፈሰ በሁለት አጋጣሚ ከርቀት ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት ተጠቀሽ ነው። በአፍሮ ፅዮን በኩል ጥሩ የተንቀሳቀሰው አምበሉ እንድርያስ ለገሰ ከግብጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው የጎል ማግባት አጋጣሚ ተጠቃሽ ሆነው የሚያልፉ የመጀመርያው አጋማሽ ሙከራዎች ናቸው።

ከዕረፍት መልስ በመጀመርያው አጋማሽ ከነበራቸው የተሻለ እንቅስቃሴ በሁለተኛው አጋማሽ ወርደው የታዩት አፍሮ ፅዮኖች ተቀዛቅዘው ታይተዋል። በአንፃሩ የሀዋሳው አሰልጣኝ ብርሃኑ ወርቁ የወሰዱት የተጫዋች ቅያሪ ተሳክቶላቸው በ55ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው እና አምና በታዛንያ በተካሄደው የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ ከፍተኛ ጎል በማስቆጠር በውድድሩ ላይ ተሸላሚ የነበረው ምንተስኖት እንድርያስ ከግራ መስመር የተጣለለትን ከተከላካዮች ጀርባ ኳሱን በመጠበቅ በቀጥታ ወደ ጎል በመምታት የሀዋሳን የመጀመርያ ጎል አስቆጥሯል። ምንተስኖት ተቀይሮ ከገባ በኋላ በአፍሮ ፅዮን ተከላካዮች ቁጥጥር ስር የነበረው መስፍን ታፈሰ ነፃነት አግኝቶ መጫወት በመቻሉ በ58ኛው ደቂቃ ከተሻጋሪ ኳስ ያገኘውን የጎል አጋጣሚ በግንባሩ በመግጨት ወደ ጎል የሞከረው የግቡ አግዳሚ መልሶበታል።

አጥቅተው በመጫወታቸው ጎል ማስቆጠር የሚገባቸው ሀዋሳዎች በአንድ ደቂቃ ልዩነት በሁለት ተስፋኛ አጥቂዎቻቸው አማካኝነት ሁለት ጎሎችን አስቆጥረዋል። 80ኛው ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ውስጥ የገባው ምንቶስነት እንድርያስ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ወድያውኑ በመልሶ ማጥቃት የተጣለለትን ኳስ መስፍን ታፈሰ በፍጥነቱ ተጠቅሞ በጥሩ አጨራረስ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በሀዋሳ 3-0 በሆነ አሸናፊነት ጨዋታው ተጠናቋል።

06:00 የተካሄደው የወላይታ ድቻ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ የጦና ንቦቹ በውድድሩ ላይ ጎልተው የወጡበትን እንቅስቃሴ በማሳየት 6-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፈው ወጥተዋል። ወላይታ ድቻዎች እስካሁን ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች በተለየ ዛሬ ተሽለው በታዩበት በዚህ ጨዋታ ጎል ማስቆጠር የጀመሩት ገና በጊዜ ነበር። በ15ኛው ደቂቃ በወላይታ ድቻ በኩል ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋቾች ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው ንጉሴ ተከስተ ከተሻጋሪ ኳስ በግንባሩ በመግጨት የመጀመርያውን ጎል አስቆጥሯል። ከባለፉት ጨዋታዎች የተሻለ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ዐፄዎቹ በጎል ሙከራ ያልታጀበ በመሆኑ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተቸግረዋል። ሚኪያስ ዘሪሁን ያደረገው ሙከራም በጨዋታው የፈጠሩት ተጠቃሽ እድል ነበር። ማጥቃታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ድቻዎች በዕለቱ በግሉ ጥሩ ሲንቀሳቀስ በዋለው አበባየሁ አዲሱ አማካኝነት በ28ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችለዋል።

ወላይታ ድቻዎች ሙሉ ለሙሉ በልጠው የተጫወቱበት የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጨማሪ አራት ጎሎች የተመለከትንበት ነበር። ከብዙ የጎል ዕድል መፍጠር በኋላ 62ኛው ደቂቃ በጥሩ አጨራረስ ብቃት የተቀበለውን ኳስ ታምራት ስላስ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። ከዚህ ጎል መቆጠር በኃላ የወላይታ ድቻን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ያቃታቸው ፋሲሎች ተጨማሪ ጎሎች ተቆጥሮባቸዋል። 68ኛው አበባየሁ አዲሱ ለቡድኑ አራተኛ ለራሱ ሁለተኛ ጎል በግሩም ቅብብል ሳጥን ውስጥ ገብቶ ሲያስቆጥር ከአንድ ደቂቃ በኋላ ተስፈኛው አጥቂ ታምራት ስላስ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አምስተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል። ሌሎች ጎል መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን መጠቀም ባይችሉም በመጨረሻም 89ኛው ደቂቃ ላይ አበባየሁ አዲሱ በጥሩ ሁኔታ የተቀበለውን ኳስ ተረጋግቶ ባስቆጠረው ጎል ለራሱ ሐት-ትሪክ ሲሰራ ጨዋታውም በወላይታ ድቻ ፍፁም የበላይነት 6-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

08:00 በተካሄደው የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በመከላከያን ከአዳማ ከተማ አገናኝቶ መከላከያ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በለመዱት ሜዳ እንዲሁም በደጋፊዎቻቸው ፊት እንደመጫወታቸው ባልተለመደ ሁኔታ እጅግ ወርደው በውድድሩ ላይ የቀረቡት አዳማዎች በመከላከያ ብልጫ ተወስዶባቸው ነው የተሸነፉት። መከላከያዎችም ጎል ማስቆጠር የጀመሩት በ14ኛው ደቂቃ በአምበላቸው አቤል ነጋሽ አማካኝነት ነበር። ከዚህች ጎል መቆጠር በኃላ መከላከያዎች ሌላ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን አጋጣሚ መሐመድ አበራ እና አቤል ነጋሽ አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀሩ እንጂ የጎል እድላቸውን ማስፋት በቻሉ ነበር።

ከእረፍት መልስ በተወሰነ መልኩ ተነቃቅተው የነበሩት አዳማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት እያደረጉ ባለበት ሁኔታ በ53ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን መሐመድ አበራ በግንባር በመግጨት የመከላከያን ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ የአዳማን እንቅስቃሴ አድክሞታል። ጦረኞቹ እንደሚያስቆጥሩት ጎል ሁሉ ያገኙትን የጎል አጋጣሚ ያለመጠቀም ችግር ቢኖርባቸውም 69ኛው ደቂቃ በመከላከያ በኩል ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው ሰለሞን ሙላው ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ የጎል መጠናቸው አስፍተዋል። በጨዋታ እንቅስቃሴ ጎል ማስቆጠር የተቸገሩት አዳማዎች በዕለቱ ዳኛ አጨቃጫቂ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ናርዶስ በአግባቡ በመጠቀም ወደ የአዳማን ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል። በመጨረሻም 85ኛው ደቂቃ ላይ መሐመድ አበራ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመትታት በግሩም ሁኔታ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በመከላከያ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቀጣይ ጨዋታዎች
ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2011
04:00 | አዳማ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ
06:00 | መከላከያ ከ አፍሮ ፅዮን
08:00 | ወላይታ ድቻ ከ ሀዋሳ ከተማ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡