ሴቶች ዝውውር | መከላከያ አዲስ አሰልጣኝ ሲሾም አምስት ተጫዋቾችን አስፈርመ

በሴቶች እግርኳስ ጠንካራ ተፎካካሪ ከሚባሉት ክለቦች አንዱ የሆነው መከላከያ አዲስ አሰልጣኝ በመቅጠር በዛሬው ዕለት ደግሞ የአምስት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል፡፡

ክለቡ የሴት ቡድኑ አሰልጣኝ በማድረግ ሰለሞን ታደለ (ቲታን) በዋና አሰልጣኝነት መሾሙን የክለቡ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ደረጀ መንግክቱ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡ አሰልጣኙ ከዚህ ቀደም በመከላከያ የታዳጊ ቡድኖች እና በዋናው ቡድን ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ሰርቷል።

ለመከላከያ ፊርማቸውን ካኖሩት ውስጥ ታሪኳ በርገና አንዷ ናት፡፡ የብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ የሆነችው ታሪኳ በ2007 ከትምህርት ቤቶች ውድድር የተገኘች ሲሆን በድሬዳዋ ሁለት ዓመታትን ካሳለፈች በኋላ ወደ ጥረት ኮርፖሬትአምርታ እስከ ውድድር ዘመኑ ፍፃሜ ቆይታ አድርጋለች።

አይዳ ዑስማን ሌላዋ የመከላከያ አዲስ ተጫዋች ሆናለች፡፡ ከመላው ኢትዮጵያ ውድድር ላይ ቤንሻንጉልን ወክላ ሀዋሳ ላይ በነበረ ውድድር ባሳየችው አስደናቂ ብቃት በአሰልጣኝ በሀይሏ ዘለቀ የወቅቱ የሲዳማ ቡና ቡድን ውስጥ ተካታ መልካም ዓመትን በማሳለፏ ወደ አዳማ ከተማ ከዛም በ2011 ደግሞ በድሬዳዋ በማምራት ለሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪነት ተፎካካሪ በመሆን ዓመቱን አጠናቃለች፡፡

ትዕግስት ዳዊት ለመከላከያ ለመጫወት የተስማማች ሦስተኛ ተጫዋች ሆናለች ፡፡ ከ2005 ጀምሮ በሀዋሳ ክለብ ውስጥ እስከ 2010 ድረስ በቀኝ መስመር ተከላካይ እና አጥቂ ስፍራ ላይ መልካም ጊዜያትን ያሳለፈች ሲሆን ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ እግር ኳሱ መመለሷን ያረጋገጠችበትን ዝውውር ፈፅማለች፡፡

ሌሎች መከላከያን የተቀላቀሉት ፀጋ ንጉሴ (ተከላካይ አ/አ ከተማ) እና ከዚህ ቀደም በደደቢት እና አዲስ አበባ ከተማ የተጫወተችው ህይወት ረጉ ሲሆኑ ያለፉትን ሶስት ዓመታት ሀዋሳ ከተማን ለቃ በመከላከያ ድንቅ የቀኝ መስመር ተጫዋች መሆኗን ያስመሰከረችው ምህረት መለሰ እና አጥቂዋ መዲና ዐወል ውላቸውን ለሁለት ዓመት ያራዘሙ ሆነዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ