ሴቶች 2ኛ ዲቪዚዮን | ቦሌ መሪነቱን የያዘበትን ድል ሲያስመዘግብ ንፋስ ስልክ እና ቂርቆስ አቻ ተለያይተዋል

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን 5ኛ ሳምንት ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ሲጀምር ቦሌ ተከታታይ ድሉን በማሳካት በጊዜያዊነት የሰንጠረዡ አናት ላይ ተቀምጧል። የንፋስ ስልክ ላ/ክ/ከተማ እና ቂርቆስ ክ/ከተማ ጨዋታ ደግሞ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

09:00 በጀመረው የመጀመርያ ጨዋታ ቦሌዎች አካዳሚን 5-1 ማሸነፍ ችለዋል። ፍፁም በሚባል ደረጃ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ለጎል የቀረበ ሙከራ በማድረግ ልዩ የነበሩት ቦሌዎች ጎል ማስቆጠር የጀመሩት ገና በ8ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ግብ ጠባቂዋ ሮማን አምባዬ ስትተፋው የቦሌዋ ተከላካይ ከአምላክነሽ ሀንቆ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኗን ቀዳሚ አድርጋለች።

ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻሉ የመጡት ቦሌዎች ከወገብ በላይ የሚገኙት ቤተልሔም ምንተሎ፣ ህዳት ካሣ፣ ሜሮን አበበ እና ሜላት ጌታቸው የነበራቸው ብቃትና ጥምረት በአካዳሚ ሜዳ ላይ እንዲፈነጩ አድርጓቸዋል። ቦሌዎች በዚህ እንቅስቃሴያቸው ተጨማሪ ጎሎችን ያስቆጥራሉ ተብሎ ቢጠበቅም በአጋማሹ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ባለመፍጠራቸው ሳይሳካ ቀርቷል። ብልጫ የተወሰደባቸው አካዳሚዎች ወደ ፊት ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት ከሁለት ቅብብል የማያልፍና ወድያውኑ የሚቋረጥ መሆኑ ምንም መፈየድ ሳይችሉ ቢቀርም የእረፍት ሰዓት መውጫ ላይ በ45ኛው ደቂቃ ዮርዳኖስ ታሪኩ ከሳጥን ውጭ ባስቆጠረችው ጎል አቻ መሆን ችለዋል።

ከእረፍት መልስ የቦሌዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በጎል የታጅበ ሆኖ ሲቀጥል በ57ኛው ደቂቃ ከመስመር የተቀበለችውን ኳስ ቤተልሔም ምንተሎ ወደ ጎልነት በመቀየር ሁለተኛ ጎል አስቆጥራለች። ብዙም ሳይቆይ በጥሩ ቅብብል ወደ ፊት የሄዱት ቦሌዎች አጥቂዋ ህዳት ካሳ ተከላካዮችን በማለፍ ወደ ጎል የመታችውን ግብጠባቂዋ ሮማን እንደምንም ያወጣችባት እንዲሁም ሜሮን አበበ በአስገራሚ ምት የግቡ አግዳሚ የመለሰባት ለቦሌዎች ጎል መሆን የሚችሉ ሌሎች አጋጣሚዎች ነበሩ።

አካዳሚዎች ሜዳ ውስጥ አልነበሩም ቢባል ማጋነን ባልሆነበት በዚህ ጨዋታ ለቦሌዎች 69ኛው ደቂቃ ፍጥነቷን ተጠቅማ ሦስተኛ ጎል ህዳት ካሣ አስቆጥራለች። የውድድሩ ኮከብ ጎል አግቢነትን በአምስት ጎል እየመራች የምትገኘው እና በሊጉ ድንቅ ብቃቷን እያሳየች የምትገኘው ወጣቷ አጥቂ ህዳት በድጋሚ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ አራተኛ ጎል አስቆጥራ የጎል መጠኑን ማስፋት ችላለች።
በመጨረሻም የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ተቀይራ የገባችው ባንቺ መገርሳ ከርቀት ባስቆጠረችው የማሳረጊያ አምስተኛ ጎል ጨዋታው በቦሌዎች የበላይነት 5-1 እንዲጠናቀቅ ሆኗል።

በመቀጠል 11:00 በተካሄደው ሁለተኛ ጨዋታ የንፋስ ስልክ እና ቂርቆስ እንደ መጀመርያው ጨዋታ ብዙም ሳቢ ያልነበረ ሆኖ ያለ ጎል ተጠናቋል። የጨዋታው መጠናቀቂያ 15 ደቂቃዎች ሲቀሩት የነበረው የፉክክር መንፈስ ተቀዛቅዞ ጨዋታውን ሲከታተል ለነበረው ተመልካች አዝናኝ ነበር።

በሁለቱም በኩል ጎል ለማስቆጠር ክፍት በነበረው የመጨረሻ ደቂቃ የጨዋታው እንቅስቃሴ ተቀይራ ገባችው የቂርቆስ አጥቂ እዩ ጌታቸው በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ፊት በመሄድ ሳጥን ውስጥ ገብታ በቀጥታ ወደ ጎል የመታችው እና የግቡ አግዳሚ የመለሰባት ኳስ ለቂርቆሶች በጨዋታው ሦስት ነጥብ ሊያገኙበት የሚችል የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። በአንፃሩ በጥሩ የኳስ ፍሰት ወደ ቂርቆስ የግብ ክልል ይድረሱ እንጂ ካለመረጋጋት የሚያበላሹት ኳሶች ንፋስ ስልኮችን ውጤታማ ሳያደርጋቸው ቀርቶ ጨዋታው ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ