ፋሲል ከነማ ሁለት አዲስ ተጫዋቾች ሲያስፈርም አንድ ተጫዋቾች ለማስፈረም ተቃርቧል

ዐፄዎቹ በቀጣይ የውድድር ዓመት ተጠናክርው ለመቅረብ ውል የጨረሱ ተጫዋቾች ውል በማደስ እንዲሁም አዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም በዝውውር መስኮቱ በመስከረም ወር እስኪከፈት ድረስ ቀድመው የቤት ሥራቸውን እየሰሩ ይገኛሉ።

ቀደም ብለው የሱራፌል ዳኛቸው፣ የአንበሉ ያሬድ ባየ፣ ከድር ኩሊባሊ፣ ሀብታሙ ተከስተ እና ሰዒድ ሐሰን ውል ያረዘሙት ፋሲል ከነማዎች ከዚህ ቀደም በቃል ደረጃ ተስማምተው የነበሩት ሽመክት ጉግሳ እና በዛብህ መለዮን ውል ማደሳቸው ታውቋል።

አዳዲስ ተጫዋቾች በማስፈረም ረገድ ግርማ ደሲሳን ያስፈረሙት ፋሲሎች ዛሬ ደግሞ ይድነቃቸው ኪዳኔ እና ፍቃዱ ዓለሙን አስፈርመዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና እና መከላከያ እንዲሁም የኢትዮጵያ የብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ ወደ ፋሲል ለመቀላለቀል ከጫፍ መድረሱን ከዚህ ቀደም መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን ለሁለት ዓመታት ቡድኑን መቀላቀሉ ታውቋል። ይድነቃቸው የ2012 ውድድር ዓመት እስከተቋረጠበተረ ጊዜ ድረስ በወልቂጤ ከተማ ቆይቷል።

ፍቃዱ ዓለሙን ከመከላከያ ሌላኛው ፋሲል ከነማን የተቃላቀለ ተጫዋች ነው። የቀድሞው የድሬዳዋ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ አጥቂ በመለካከያ ያለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት የቆየ ሲሆን በመከላከያ እና አዲስ አበባ አብረውት ከሰሩት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ጋር በድጋሚ ተገናኝቷል።

ከኢትዮጵያ ቡና ወጣት ቡድን አድጎ ቡድኑን በአምበልነት ሲመራ የቆየው አማኑኤል ዮሐንስ በቡናማዎቹ ቤት ለመቆየት ከስምምነት መድረሱ ቢነገርም ወደ ጎንደሩ ክለብ ለማምራት ከጫፍ ደርሷል። ተጫዋቹ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ መስማማት ከቻለ ለቀጣይ ሁለት ዓመታት የዐፄዎቹን መለያ ለመልበስ ቅድመ ኮንትራት የሚፈርም ይሆናል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ