የሴቶች ገፅ | አምባሳደሯ ተጫዋቾች እንዳይጠፉ የተጠቀሙት አስገራሚ ስልት…

ለ2012 የለንደን ኦሊምፒክ ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ የነበሩት ሉሲዎቹ በደቡብ አፍሪካ ለመጥፋት አቅደው በጊዜው በነበሩ አምባሳደር አስገራሚ ስልት ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል። ይህንን አስገራሚ ገጠመኝንም አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው መለስ ብሎ አጫውቶናል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ለ2012 የለንደን ኦሊምፒክ ለማለፍ ጫፍ ደርሶ እንደነበር ይታወሳል። በተለይ ቡድኑ ጋናን በደርሶ መልስ ውጤት ረትቶ 180 ደቂቃዎችን ብቻ ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር በመፋለም ወደ ኦሊምፒክ ውድድር ለማለፍ ተቃርቦ ነበር። በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው እየተመራ የነበረው ቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለማድረግ ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንቶ 3-0 ቢሸነፍን በጊዜው አነጋጋሪ የሆነ ክስተት ከጨዋታው መገባደድ በኋላ እንደተፈፀመ ይነገራል። ይህንን ክስተትም ለ7 የተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድንን ሲያሰለጥን የነበረው እና ከክለቡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ስኬትን እያጣጣመ የሚገኘው ብርሃኑ ግዛው መለስ ብሎ አውግቶናል።

በ21 ዓመታት የአሰልጣኝነት ቆይታው 21 ዋንጫዎችን ያገኘው ብርሃኑ ትዝታውን ሳቅ በተቀላቀለበት ንግግሩ ጀምሯል። “በጊዜው እኔ ለብሄራዊ ቡድኑ አዲስ ነበርኩ። ግን ቡድኑ ውስጥ የነበረው ፍቅር፣ አንድነት እና መተሳሰብ ብሄራዊ ቡድኑ ለረጅም ጊዜ አብሮ የቆየ አስመስሎት ነበር። ጊዜው ለለንደን ኦሎምፒክ ለማለፍ ጫፍ የደረስንበት ነበር። ኮንጎ እና ጋናን በጥሩ የጨዋታ ብልጫ አሸንፈን ወደ ኦሎምፒኩ ለማለፍ 180 ደቂቃዎች ብቻ ቀሩን። በዚህም የመጨረሻ ተጋጣሚያችን ደቡብ አፍሪካ ሆነች። የሚገርምህ ለጨዋታው ለ2 ወራት ጠንካራ ዝግጅት አድርገን ነበር። ነገር ግን ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንተን 3-0 ተሸነፍን። እርግጥ በጨዋታ የእኛ ቡድን ድንቅ ነበር። ግን ደቡብ አፍሪካዎች ጎሎችን አስቆጥረውብን ውጤቱን ከባድ አደረጉብን።”

ጨዋታው ካለቀ በኋላ አብዛኛው የቡድን ስብስብ ዐምሮ ውስጥ የነበረው “የመጥፋት” ነገር እጅግ እየጨመረ እንደመጣ የሚናገረው ብርሃኑ ልዑካኑ ግራንድ ኮርት ወደ ተባለ ሆቴል ሲያመራ የቡድኑ አምበል ዘይቱና ያሲን ከስብስቡ ጠፍታ እንዳመለጠች ያስታውሳል። በዚህም አጋጣሚ በርካታ ተጫዋቾች እንዴት እና መቼ መጥፋት እንዳለባቸው በይበልጥ ማውጠንጠን ቀጠሉ። አሰልጣኙም ለተሻለ ህይወት ወደ ሌላ ሃገር ለማምራት ዝግጅቶችን ማድረግ እንደቀጠለ ያወሳል። “በጊዜው ተጫዋቾቻችን እንዳይጠፉ ለሊት ለሊት እንጠብቃቸው ነበር። ነገር ግን ከጨዋታው በኋላ የአብዛኛው የቡድን አባል ሃሳብ አንድ ሆነ። መጥፋት። የእኔም ወንድም ወደ ኬፕታውን ሊወስደኝ ማረፊያችን ድረስ መጣ። ብቻ ሁሉም በየፊናው የሚጠፋበትን መንገድ ማሰብ ቀጠለ።”

“ጊዜው ደረሰና ከሆቴል ወጥተን ወደ አየር ማረፊያ ለማምራት ወደ ባስ እየገባን እያለ ከመሃላችን ኤደን ሽፈራውም ዘላ ጠፋች። እርግጥ አብዛኞቻችን ወደ አየር ማረፊያ ስንሄድ ለመጥፋት ብናስብም የሷ ቀድሞ መሰወር አስደነገጠን። ይባስ ብሎ ሌላ ያልጠበቅነው ነገር ገና እግራችን ባሱን እንደረገጠ ተከሰተ። በጊዜው በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑ ግለሰብ በአንድ የፖሊስ መኪና ታጅበው መጡና ባስ ውስጥ ገቡ። አምባሳደሯ የአብዛኛውን የቡድን አባል ሃሳብ አውቀው ስለነበር አጭር ትዕዛዝ አስተላለፉልን። ‘አብዛኞቻችሁ እዚህ ልትጠፉ እንደሆነ አውቄያለሁ። ይህንን አደለም ማድረግ ማሰብ እራሱ የለባችሁም። ይህቺ ሃገር በጣም መጥፎ ሃገር ናት። በተለይ ለሴቶች አትሆንም። ከኢትዮጵያ አብራችሁ የመጣችው ዘይቱና ያሲን ትናንት ጠፍታ እንደነበረ ታውቃላችሁ። ነገርግን መጨረሻዋ በብዙ ወንዶች መደፈር ሆኗል። ተጫዋቿ ከኋላ የምትመለከቱት የፖሊስ መኪና ውስጥ አለች። በጣም ስለተጎዳች እናንተን አሁን ማግኘት አትችልም። ግን አውሮፕላን ላይ እንድትቀላቀላችሁ እናደርጋለን። ስለዚህ እዚህ ብትጠፉ መጨረሻችሁ አያምርም። ይቅርባችሁ!’ አሉን። በዚህም በጣም ደነገጥን። በመኪና ውስጥ የነበረው ሁሉም የቡድኑ ልዑካን ሃሳቡን ወዲያው ቀየረ። እኔም ወንድሜን ትቼ ወደ ሃገሬ ለመመለስ እዛው መኪና ውስጥ ወሰንኩ። ከዛ ወደ አየር ማረፊያ በቀጥታ አመራን። ፍተሻ እና የተለያዩ ነገሮችን ካከናወንን በኋላ አውሮፕላን ውስጥ ገባን። እስከዚህ ሰዓት ድረስ የጠፋችው እና ተደፍራለች የተባለችው አምበላችን ዘይቱና አልተቀላቀለችንም። የፕሌኑን በር ብናይ፣ ብናይ ተጫዋቿ አልመጣ አለች። አውሮፕላኑ ሲነሳ ግን አምባሳደሯ እንደሸወዱን ገባን። እኛ እንዳንጠፋ የፈጠሩት ሃሳብ እንደሆነ ደረስንበት።”

በአምባሳደሯ ስልት ወደ ሃገራቸው የተመለሱት ሉሲዎቹ በድምር ውጤት በደቡብ አፍሪካ ተረተው ለኦሊምፒክ ውድድር ሳይበቁ ቀሩ። ምንም እንኳን ቡድኑ ለውድድሩ ባይበቃም በጊዜው የነበሩት ክብርት አምባሳደር ልዑካኑ እንዳይጠፋ እና ወደ ሃገሩ እንዲመለስ የዘየዱት መላ አስገራሚ ሆኖ እስካሁን ይነሳል። አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛውም አምባሳደሯ የሰሩትን ስራ አሁን ላይ ሲያስበው ልክ እንደነበረ ይመሰክራል።

“አምባሳደሯ በጊዜው በጣም ትክክል ናቸው። በተለይ አሁን ላይ ሆኜ ያደረጉትን ሳስብ በጣም አደንቃቸዋለሁ። አሁን ያለሁበት ደረጃም እንድደርስ የእርሳቸው ስልት እና ብልሃት በግሌ በጣም ጠቅሞኛል። ያኔ ደቡብ አፍሪካ ብጠፋ ኖሮ አሁን ያለሁበት ደረጃ አልደርስም ነበር። ቀበቶ ነጋዴ ነበር የምሆነው (እየሳቀ)። እኔ ብቻ ሳልሆን በስብስቡ ውስጥ የነበሩ አብዛኞቹ ተጫዋቾችም አሁን ትልቅ ደረጃ ደርሰዋል። እንደውም እኔ አምባሳደሯን አሁን ላይ አግኝቼ ባመሰግናቸው ምንኛ በታደልኩ።”

ለ2012 የለንደን ኦሊምፒክ ለመብቃት ያልቻሉት ሉሲዎቹ ከጥቂት ወራቶች በኋላ ግን በአሰልጣኝ አብርሃም ተክለሃይማኖት እና ብርሃኑ ግዛው እየተመሩ ለ2012 የአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸው አይዘነጋም።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ