ቅድመ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ሰበታ ከተማ

የነገውን የመጀመሪያ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግን ጨዋታ በዳሰሳችን እንዲህ ተመልክተነዋል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና እና ምክትል ሆነው ይሰሩ የነበሩት አሰልጣኞች አብርሀም መብራቱ እና ሙሉጌታ ምህረትን ለመጀመርያ ጊዜ እርስ በእርስ የሚገናኙበት ይህ ጨዋታ የሊጉ ሁለተኛ ሳምንት ማስጀመሪያ ይሆናል።

በመጀመሪያው ሳምንት አራፊ የነበረው ሀዋሳ ከተማ በቀድሞው አምበሉ እና በምክትል አሰልጣኝነትም ባገለገለው አሰልጣኝ ሙሉጌታ መመራትን ምርጫውን አድርጎ ከህዳር አጋማሽ አካባቢ በመጀመር በዝግጅት ላይ ቆይቷል። የአብዛኛዎቹን ቁልፍ ተጫዋቾቹን ውል ያራዘመው ሀዋሳ ውስን ግን ደግሞ በሊጉ በነበሩባቸው ክለቦች በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የመካተት ታሪክ ያላቸውን ተጫዋቾች በእጁ አስገብቷል። በዝውውር ሂደቱ እንደ ግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳህ ፣ ጋብርኤል አህመድ እና ኤፍሬም ዘካርያስ ዓይነት የቀድሞው ተጫዋቾቹ ጋር በድጋሚ ሲገናኝ ዘነበ ከድር ፣ ዳግም ተፈሪ ፣ ምኞት ደበበ እና ኤፍሬም አሻሞም ዘንድሮ በሀዋሳ የምንመለከታቸው አዳዲስ ተጫዋቾች ይሆናሉ። የተጋጣሚውን ደረጃ እና የጨዋታ ምርጫ በመጀመሪያው ሳምንት የመገምገም ዕድልን ያገኘው ሀዋሳ የካስ ቁጥጥርን መሰረት ያደረገ አቀራረብ እንደሚኖረው ይገመታል። እንደመስፍን ታፈሰ ዓይነት ፈጣን አጥቂዎች ያለው በድኑ መሰል ተጫዋቾችን የማቆም ችግር ለተነበበት የሰበታ ተከላካይ ክፍል ፈተና ሊሆን እንድሚችልም ይገመታል። ቡድኑ በአመዛኙ የበፊቱን ስብስቡን ይዞ መቆየቱ የቡድን ውህደት ሂደቱን ለማገዝ እንደሚረዳው ሲታመን ተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ ካለው እና ልምድ ያካበቱ አማካዮችን ከያዘው ሰበታ ጋር ለሚኖርበት የኳስ ቁጥጥር ፍልሚያም የሚጠቅመው ይሆናል።

ሊጉን በአቻ ውጤት የጀመረው የአብርሀም መብራቱ ሰበታ ከተማ የዓመቱን የመጀመሪያ ግቡን የሚያልምበትን ጨዋታ ያደርጋል። ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት የሚሞክረው ቡድኑ በዚህ ረገድ ብዙ ተቸግሮ ባይታይም የመጨረሻ ዕድል ፈጣሪ የሆኑ አማካዮቹ ከአደጋው ክልል ራቅ ብለው እና ለራሳቸው ሜዳ ቀርበው መንቀሳቀሳቸው በርካታ የመጨረሻ ዕድሎችን እንዳይፈጥሩ በራሳቸውም ሙከራዎችን እንዳያደርጉ አግዷቸው ታይቷል። አሰልጣኝ አብርሀም “ከልምድ ማነስ እና ከትኩረት ማነስ ግብ መሆን የሚችሉ ኳሶችን መጨረስ ላይ ድክመት ነበረብን” በማለት የገለፁት ሀሳባቸውን መነሻ በማድረግም ችግሩን ለመቅረፍ ፊት መስመር ላይ የተጫዋች ለውጥ ሊያደርጉ የሚችሉበት ዕድልም ሊኖር ይችላል። ከመጨረስ ችግሩ ባለፈ ግን ቡድኑ የማጥቃት ወረዳ ላይ ሲገኝ በቁጥር ተበልጦ ክፍተቶችን እንደልቡ ማግኘት ቀላል እንዳልሆነለት የድሬው ጨዋታ የሚያሳይ ነበር። በመከላከሉም ረገድ በርካታ የግብ ሙከራዎችን ባስተናገደበት የመጀመሪያ ጨዋታ የኋላ መስመር ተሰላፊዎቹ ከፈጣን አጥቂዎች ጋር አንድ ለአንድ ሲገናኙ ተቸግረው መታየታቸው ለነገው ጨዋታ እንደ ስጋት የሚታይ ሌላው ነጥብ ነው። ያም ቢሆን ፍፁም ቅጣት ምትን ጨምሮ ያለቀላቸው ግቦችን ያዳነው የግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ድንቅ ብቃት ነገም የሀዋሳ አጥቂዎችን ጥረት በማክሸፍ ይደገም ይሆን ? የሚለው ጥያቄ ምላሽ በጉጉት የሚጠበቅ ይሆናል።

በጨዋታው በሀዋሳ ከተማ በኩል ወጣቱ አጥቂ ሀብታሙ መኮንን በጉዳት ሳቢያ ከጨዋታ ውጪ እንደሆነ የተሰማ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ቅጣቱ ወደ ዘንድሮ የዞረው አለልኝ አዘነም አይኖርም። በሰበታ በኩል ደግሞ ሦስት ተጫዋቾች በኮቪድ 19 ተይዘው አሁን ላይ በመልካም ጤንነት ላይ ቢገኙም በለይቶ ማቆያ ውስጥ በመሆናቸው ለነገ እንደማይደርሱ ለማወቅ ችለናል። 

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በሊጉ ከዚህ ቀደም ለስድስት ጊዜያት ተገናኝተው ሰበታ 3 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ሀዋሳ 1 ድል አስመዝግቧል። በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል።

– በስድስቱ ጨዋታዎች ሰበታ 5 ሲያስቆጥር ሀዋሳ 4 አስቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ዳንኤል ደርቤ – ላውረንስ ላርቴ – ምኞት ደበበ – ደስታ ዮሃንስ

ሄኖክ ድልቢ – ጋብርኤል አህመድ – ዘላለም ኢሳይያስ

ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ – ኤፍሬም አሻሞ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ፋሲል ገብረሚካኤል

ዓለማየሁ ሙለታ – መሳይ ጳውሎስ – ቢያድግልኝ ኤልያስ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

ዳዊት እስጢፋኖስ – መስዑድ መሀመድ – ፉዓድ ፈረጃ

ታደለ መንገሻ – እስራኤል እሸቱ – ቡልቻ ሹራ


© ሶከር ኢትዮጵያ