“የጎደሉብንን አሟልተን ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን” – ወንድማገኝ ማርቆስ

ጅማ አባ ጅፋር እስከ አራተኛ ሳምንት ድረስ በአንድ ጨዋታ ካገኘው አንድ ነጥብ ውጭ ድል ቢርቀውም በግሉ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ከሚገኘው ከወንድማገኝ ማርቆስ ጋር ቆይታ አድርገናል።

የእግርኳስ መነሻው ያደረገው በትውልድ ከተማው በሚገኘው ጅማ አባ ቡና ነው። ከታዳጊ ቡድን ጀምሮ መጫወት የቻለው ወንድማገኝ ያለፉትን ሁለት ዓመት ወደ ጅማ አባ ጅፋር በመቀላቀል መልካም የሚባል የእግርኳስ ህይወቱን እየመራ ይገኛል። በ2013 የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት በደረሰበት በአሁኑ ወቅት ጅማ አባ ጅፋር ምንም እንኳን በውጤት ቀውስ ውስጥ ቢገኝም ወንድማገኝ በአራቱም ጨዋታ ላይ የቡድኑ ቋሚ ተሰላፊ በመሆን በግሉ ጥሩ አቋሙን እያሳየ ከሚገኝ ሲሆን ስለ ቡድኑ ቀጣይ ሁኔታ እና በግሉ እያደረገ ስለሚገኘው እንቅስቃሴ ከዛሬው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አግኝተን ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቶናል።

” በቡድናችን ዝግጅት የጀመረው ዘግይቶ ነው። በዛ ላይ የወዳጅነት ጨዋታ አላደረግንም። በዚህም ቡድኑን መገንባት አልቻልንም። የተጫዋቾች ዝውውርም በፌዴሬሽኑ በኩል ዘግይቶ ነው የፀደቀልን፤ ይህ ተፅእኖ አድርጎብናል። በአስተዳደር በኩል ያልተሟላ የደሞዝ ችግር አለብን። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተደምረው ቡድናችንን በስነ ልቦናው እንዲወርድ አድርጎብናል። ሽንፈትም ሲበዛ ይታወቃል ማገገም ከባድ ነው።

” በግሌ ጥሩ ነገር ለማድረግ እየሞከርኩ ነው። ጅማ ከታች ጀምሮ ያሳደገኝ ቡድን ስለሆነ የምችለውን ሁሉ ለማድረግ እየታገልኩ ነው። የቡድኑ ውጤት ምንም ሆነ ምን እኔ በግሌ የተሻለ ቦታ ለመድረስ አስባለው።

“ስለ መውረድ አሁን አላስብም። ገና የሚቀር ሀያ ጨዋታ አለ። ከዚህ በኋላ ያሉብንን ስህተቶች አስተካክለን፤ የጎደሉብንን አሟልተን ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ