ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ ቀን ውሎ መጀመሪያ የሚሆነው ጨዋታ ላይ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ወልቂጤ ከተማ የመጀመሪያ ድሉን ወላይታ ድቻ ላይ ካሳካ በኋላ የነገውን ከባድ ፍልሚያ የሚያደርግ ይሆናል። ፊት መስመር ላይ የማጥቃት ኃላፊነቱን ከአህመድ ሁሴን ወደ አብዱርሀማን ሙባረክ ያዞረው ቡድኑ አሁንም የሚፈልገውን አስፈሪነት ያገኘ አይመስልም። ያም ቢሆን በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት የጎል አካውንቱን የከፈተው ወጣቱ ያሬድ ታደሰ የደረሰለት ይመስላል። የያሬድ በግብ ፊት በራስ መተማመን እና ጥብቅ የሆኑት ምቶቹ በነገው ጨዋታ ላይ የሚፈጥሩት ልዩነትም ከወዲሁ ተጠባቂ ሆኗል። በተከላካይ እና በአማካይ ክፍል መሀል ክፍተት ባለመስጠት የማይታማው ግን ደግሞ ነገ ያለሳምሶን ጥላሁን የሚገባው የባህርዳር አጨዋወት ውስጥ የወልቂጤ አማካዮች የግብ ዕድል በመፍጠሩ ረገድ ከባድ ፍትጊያ እንደሚጠብቃቸው ሲገመት ይህኛው የሜዳ ክፍል ላይ የሚኖረው ፉክክር የጨዋታውን ውጤት የመወሰን አቅሙ ከፍ ያለ ነው። ከዚህ ውጪ የሰራተኞቹ የማጥቃት መንፈስ የሚቀዛቀዙባቸው ቅፅበቶች ቡድኑን ለመልሶ መጠቃት እንዳያጋልጠው ያሰጋዋል። በዚህ ረገድ የቡድኑ የማጥቃት አማካዮች በሀብታሙ ሸዋለም ግራ እና ቀኝ የሚኖሩ እንቅስቃሴዎችን በቶሎ የማቋረጥ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል።

በሀዲያ ሆሳዕና እና አዳማ ከተማ ጨዋታዎች የተለያየ መልክ የተስተዋለበት ባህር ዳር ከተማ ሦስተኛ ድሉን አሳክቶ ከተፎካካሪ ቡድኖች ጋር ለመስተካከል ከፊቱ ወልቂጤ ይጠብቀዋል። ባህር ዳር በነገውም ጨዋታ ከፍ ባለ የጨዋታ ግለት በመጀመር በቶሎ ግቦችን ለማግኘት የሚረዳውን እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። በቅብብሎች በቶሎ ግብ ጋር ለማድረስ በሚያልመው የቡድኑ የጨዋታ ሂደትም በሦስቱ ማጥቃት ባህሪ ባላቸው አማካዮቹ እና በመስመር ተከላካዮቹ አጋዥነት የሜዳውን ስፋት በመጠቀም ጥቃት እንደሚሰነዝር ይታሰባል። ይህ የቡድኑን አካሄድ ለመቋረጥ የወልቂጤ መሀል ክፍል ምላሽ ምን እንደሚሆንም ከጨዋታው የሚጠበቅ ነው። የመሀል ሜዳውን ፈተና አልፈው የተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ከተገኙ ግን ባህር ዳሮች የተሻለ የአጨራረስ ብቃት እንደሚኖራቸው ካለፉት ጨዋታዎች መረዳት እንችላለን።

ባህር ዳር ከተማ በአዳማው ጨዋታ ተጎድቶ የወጣው ወሳኝ አማካዩ ሳምሶን ጥላሁንን ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን አቤል ውዱም ጉዳት ላይ ይገኛል የአፈወርቅ ኃይሉ ማገገም ደግሞ ለቡድኑ መልካም ዜና ሆኗል። በወልቂጤ በኩል ደግኖ ባለፈው ጨዋታ ተቀይሮ መግባት ችሎ የነበረው አጥቂ ሄኖክ አየለ ፣ ዳግም ንጉሴ እና ሙኸጅር መኪ ጉዳት ላይ እንደሆኑ ሰምተናል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ በተሰረዘው የውድድር ዓመት ባደረጉት ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ የ 2-0 ድልን ማሳካት ችሎ ነበር። የነገው ፍልሚያ ግን የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ግንኙነታቸው ሆኖ ይመዘገባል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ጀማል ጣሰው

ተስፋዬ ነጋሽ – ቶማስ ስምረቱ – አሚን ነስሩ – ረመዳን የሱፍ

በኃይሉ ተሻገር – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ

ፍሬው ሰለሞን – አህመድ ሁሴን – ያሬድ ታደሰ

ባህር ዳር ከተማ (4-2-3-1)

ሀሪሰን ሄሱ

ሚኪያስ ግርማ – ሰለሞን ወዴሳ – መናፍ ዐወል – አህመድ ረሺድ

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – በረከት ጥጋቡ

ዜናው ፈረደ – ፍፁም ዓለሙ – ግርማ ዲሳሳ

ባዬ ገዛኸኝ


© ሶከር ኢትዮጵያ