የኢትዮጵያ ዋንጫ | ወላይታ ድቻ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል

የጦና ንቦቹ ፈረሰኞቹን 2ለ1 በመርታት ግማሽ ፍጻሜውን የተቀላቀሉ ሁለተኛ ቡድን ሆነዋል።

በኢትዮጵያ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ሁለተኛ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ሲገናኙ 9 ሰዓት ላይ በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል ለመድረስ ፈጣን እንቅስቃሴዎችን ቢያደርጉም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ውጤታማ አልነበሩም።


በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ 18ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያው ለግብ የቀረበ ሙከራ ተደርጓል። በዚህም አማኑኤል ኤርቦ በቀኝ መስመር በተሻገረለት ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ መልሶበታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ የወላይታ ድቻው ቢኒያም ፍቅሩ ጥሩ ሙከራ አድርጎ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሊያመራ በተጨመሩ አራት ደቂቃዎች ውስጥ የመጀመሪያው ደቂቃ ላይ ድቻዎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ቢኒያም ፍቅሩ ከመሃል ብሥራት በቀለ በድንቅ ዕይታ  የሰነጠቀለትን ኳስ ከሳጥን አጠገብ በግሩም አጨራረስ መሬት ለመሬት በመምታት በግቡ የግራ ክፍል በኩል መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ከዕረፍት መልስ ፈረሰኞቹ በተሻለ ግለት ጨዋታውን ቢጀምሩም ድቻዎች 49ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ዘላለም አባተ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ቀንሶ ያመቻቸለትን ኳስ ያገኘው ብሥራት በቀለ በድንቅ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

በሁለት ግብ መመራት ከጀመሩ በኋላ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ተጭነው መጫወት የቻሉት ጊዮርጊሶች የአጋማሹን የመጀመሪያ የጠራ የግብ ዕድል 65ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ ረመዳን የሱፍ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ሲመልስበት የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ዳግማዊ አርዓያም ኃይል በሌለው የጭንቅላት ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

የጦና ንቦቹ ጨዋታውን በተሻለ የራስ መተማማን በማስቀጠል በጥቂት ንክኪዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም የመጨረሻ ኳሳቸው ፈታኝ አልነበረም። ሆኖም ግን 79ኛው ደቂቃ ላይ በቢኒያም ፍቅሩ አማካኝነት በግቡ የግራ ቋሚ በኩል የወጣ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር።

እጅግ አወዛጋቢ ክስተት በተፈጠረባቸው የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ውስጥ ፈረሠኞቹ ተደጋጋሚ ጥቃት መሰንዘር ሲችሉ 82ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ተቀይሮ የገባው ሻይዱ ሙስጠፋ በሳጥኑ የግራ ጠርዝ በግሩም ሁኔታ ያመጣውን ኳስ ከታምራት ኢያሱ ጋር ተቀባብሎ ወደ ግብ ሞክሮት የግቡ የግራ ቋሚ ሲመልስበት የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ለቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን ጨዋታ ያደረገው ታምራት ኢያሱ አስቆጥሮታል። በዚህ አጋጣሚ አንደኛ ረዳት ዳኛ የነበሩት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት ግቡን ቢሽሩትም ከዋና ዳኛው ኢንተርናሽናል ዳኛ  ኃይለኢየሱስ ባዘዘው ጋር በተደረገ ንግግር ዋና ዳኛው ግቡን አጽድቀውታል።


በከፍተኛ ውጥረት በተሞሉት የመጨረሻ ደቂቃዎች ውስጥ 90+5ኛው ደቂቃ ላይ የጊዮርጊሱ ቢኒያም በላይ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ከጥቂት ንክኪዎች በኋላ ያገኘው ታምራት ኢያሱ ቢያስቆጥረውም ኳሱ ከመለቀቁ በፊት ፍሪምፖንግ ሜንሱ ከጨዋታ ውጪ ነበር በሚል ዕምነት ረዳት ዳኛው ፋሲካ የኋላሸት ሽረውታል። ጨዋታውም በወላይታ ድቻ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ወላይታ ድቻ ከኢትዮጵያ መድን በመቀጠል ግማሽ ፍጻሜውን የተቀላቀለ ሁለተኛው ቡድን መሆኑን አረጋግጧል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እና የቡድን አባላት በዳኝነቱ ላይ እጅግ ከፍተኛ ተቃውሞ አሰምተዋል።