የእለቱ ዜናዎች ፡ ጥቅምት 15 ቀን 2010

​በእለቱ በኢትዮጵያ እግርኳስ የተሰሙ አዳዲስ መረጃዎችን እንዲህ አቅርበንላችኋል፡፡ 

ምርጫ 2010

ለፕሬዝዳንነት የሚወዳደሩ ግለሰቦች እየታወቁ ነው

ጥቅምት 30 ቀን 2010 በአዲስ አበባ ኢንተርኮንቲኔንታል የሚደረገው የፌዴሬሽኑ ምርጫ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡ እስካሁንም 4 ክልሎች በይፋ ለፕሬዝዳንትነት የወከሏቸውን ሰዎች ይፋ አድርገዋል፡፡ ደቡብ ክልል ከ1996 እስከ 2000 የፈዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት የነበሩት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር)፣ ኦሮሚያ ክልል የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ብሔራዊ ቡድን ኮከብ አንተነህ ፈለቀ፣ አማራ ክልል ከ2000-2006 የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ተካ አስፋውን እንዲሁም ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የወቅቱ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ እስካሁን ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደሩ የታወቁ ሲሆኑ ከሐረረ የተወከሉት አምባሳደር ቶፊቅ አብዱላሂ (ዶ/ር) ለመወዳደር መወሰን አለመወናቸው በቀጣይ ጊዜያት ይታወቃል፡፡ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ ኢትዮ ሶማሌ እና አፋር ለፕሬዝዳንትነት እጩዎችን እንደማይልኩ የታወቀ ሲሆን ትግራይ እና አዲስ አበባ በቀጣይ ተወካያቸውን እንደሚያሳውቁ ይጠበቃል፡፡

ለስራ አስፈፃሚነት እስካሁን ከየክልሉ የተወከሉ ግለሰቦች

አማራ – ሰውነት ቢሻው (ኢንስትራክተር)

ኦሮሚያ – አቶ ታምራት በቀለ

ደቡብ – አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ

አፋር – አቶ አሊሚራህ መሐመድ

ቤኒሻንጉል – ወ/ሮ ሶፊያ

አዲስ አበባ – ኃይለየሱስ ፍስሃ (ኢንጂነር)

ጋምቤላ – ቾል ቤል (ኢንጂነር)

የጊዜ ገደቡ ተራዝሟል

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለፕሬዝዳንትነት እና ስራ አስፈፃሚነት የሚቀርቡ እጩዎች ለማቅረብ ያቀረበው የጊዜ ገደብ ዛሬ ቢጠናቀቅም እስከ ጥቅምት 20 ድረስ አራዝሞታል፡፡ በቀጣዮቹ ቀናትም ክልሎች በሚወክሏቸው ግለሰቦች ላይ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ፕሪምየር ሊግ 

ኢትዮጵያ ቡና እና ድራጋን ፖፓዲች የመለያያቸው ጉዳይ እርግጥ እየሆነ ነው

በክረምቱ ለሁለተኛ ጊዜ ቡናን የተረከቡህ አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች በደረሰባቸው የጤና እክል ምክንያት ክለቡ የ18 ቀናት እረፍት መስጠቱ ይታወሳል፡፡ አሰልጣኙ በሀኪሞች በጤናቸው ላይ ጫና ከሚፈጥረው የማሰልጠን ስራ እንዲገለሉ መምከሩ የሚታወስ ሲሆን ሰኞ እለት በተሰጣቸው የህክምና ውጤት መሰረት ጤናቸው መሻሻል ቢያሳይም አሁንም ወደ ስራ ገበታቸው መመለስ እንደሌለባቸው ተነግሯቸዋል፡፡

አሰልጣኙ በህክምና ውጤቱ ተሰፋ የመቁረጥ ምልክት ያሳዩ ሲሆን ምናልባትም ጥቅምት 29 የመጨረሻው የህክምና ውጤት ሙሉ ለሙሉ ከአሰልጣኝነት በአሰልጣኝነት የመቀጠል እና ያለመቀጠል እጣ ፈንታቸውን ይወስናል ተብሏል፡፡

ክለቡ ለፖፓዲች ተተኪ ከሌላኛው ሰርቢያዊ ኮስታዲን ፓፒች ጋር እየተደራደረ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡

በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ጉዳይ ተጫዋቾች ሊቀጡ ይችላሉ

በኢትዮ ኤሌትሪክ እና በሀዋሳ ከተማ መካከል የተደረገውን ጨዋታ ውጤት ለማስለወጥ ሙከራ መደረጉን በመግለጽ የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፒሊን ኮሚቴ ድርጊቱን ፈፅመዋል ባላቸው ተጨዋቾች ላይ እስከ ሁለት አመት የሚደርስ ቅጣት ሊጥል ተዘጋጅቷል፡፡ ሆኖም ሙከራው ከጨዋታው በፊት በመክሸፉ በጨዋታው ላይ የታየ የውጤት ማስለወጥ ድርጊት አለማግኘቱን በመግለጽ የሀዋሳ እና የኤሌትሪክ ጨዋታ ውጤት ማፅደቁን ሰምተናል።

በተያያዘ ዜና የፀረ ሙስና ኮሚሽን የጨዋታ ማጭበርበር ተፈፅሟል ተብሎ የቀረበለትን የሰነድ ማስረጃ እንዲሁም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን አካላት በማነጋገር ያቀረበውን ሰነድ አቃቤ ህግ ተመልክቶ ጉዳዩ በህግ ያስከስሳል ወይስ አያስከስስም የሚለውን ዛሬ ውሳኔ መስጠቱ ተነግሯል። (ውሳኔውን እንደደረሰን እናቀርባለን)

ፌዴሬሽኑ የአክሊሉን ይግባኝ ውድቅ አድርጓል

የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን ኮሚቴ አስቀድሞ ለፋሲል ከተማ በኋላ ለኢትዮዽያ ቡና የፈረመው አክሊሉ አያነው ለፋሲል ከተማ 600 ሺህ ብር እንዲከፍል መቀጣቱን ተከትሎ ያቀረበው የይግባኝ ጥያቄ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውድቅ ማድረጉ ታውቋል። ይህን ተከትሎም አክሊሉ ፋሲል ከተማ ይቅርታ እንዲያደርገለት ጥያቄ ማቅረቡ ተሰምቷል፡፡

ከፍተኛ ሊግ

ኢትዮጵያ መድን ናይጄርያዊ አጥቂ አስፈረመ

የከፍተኛ ሊጉ ክለብ ኢትዮጵያ መድን ናይጄርያዊው አጥቂ አዳም ሳሙኤልን አስፈርሟል፡፡ በሃገሩ ክለብ ኤኤሲሲ ሲጫወት የቆየው ሳሙኤል የአንድ አመት ኮንትራት የፈረመ ሲሆን ትላንት ቡድኑ ከጅማ አባ ቡና ጋር ባደረጉት ጨዋታ ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡

ነቀሞት ከተማ ንግድ ባንክን ሊተካ?

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡድኑን ማፍረሱን ተከትሎ የተለያዩ አካላት ክለቡ ውሳኔውን እንዲቀይር ያደረጉት ጥረት የተሳካ አይመስልም፡፡ በ2009 ከከፍተኛ ሊጉ ከወረዱ 6 ክለቦች መካከል የተሻለ ነጥብ ያስመዘገበው ነቀምት ከተማም ንግድ ባንክን እንደሚተካ ተነግሯል፡፡

ከፍተኛ ሊጉ ሊራዘም ይችላል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2010 የውድድር ዘመን ጥቅምት 25 እንደሚጀመር ቢገለፅም ሊራዘም እንደሚችል ተነግሯል፡፡ የደቡብ እግርኳስ ፌዴሬሽን ውድድሩ እንዲራዘም ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱ የካስቴል የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ዋንጫን ከመስከረም 19-27 ለማድረግ እንደወሰነ ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡

ሴቶች ፕሪምየር ሊግ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሴቶች ቡድን ተጨማሪ ተጫዋቾች አስፈርሟል

ቅዱስ ጊዮርጊስ የሴቶች ቡድን ተጨማሪ 5 ተጫዋቾችን ማስፈረሙን አስታውቋል፡፡ የመከላከያዋ ፍቅርተ ብርሃኑ ፣ እንዲሁም የጥረቶቹ ወርቅነሽ መልሜላ ፣ ኪፊያ አብዱራህማን ፣ ፍቅርተ አስማማው እና ቤትሄም ሰማን ከልቡን በአንድ አመት ውል ክለቡን ተቀላቅለዋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዚህ ቀደም ሰሚራ ከማል፣ እታፈራሁ አድርሴ ፣ ቱቱ በላይ እና ቤዛዊት ተስፋዬን ማስፈረሙ የሚታወስ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በውጪ

በአልባንያ ሱፐር ሊጋ 7ኛ ሳምንት ቢንያም በላይ የሚጫወትበት ስከንደርቡ ኬኤፍ ከሜዳው ውጪ ቱታ ዱረስን ገጥሞ 4-1 አሸንፏል፡፡ በጨዋታው ላይ ቢንያም በላይ በተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበረ ሲሆን ተቀይሮ ሳይገባ ጨዋታው ተጠናቋል፡፡ ስከንደርቡ ጨዋታውን ማሸነፉን ተከትሎ ሉጉን በ19 ነጥቦች ከተታዩ ኩርሲ በ3 ነጥቦች ቀድሞ መምራቱን ቀጥሏል፡፡

አፍሪካ

አል አህሊ ለመንግስት ጥያቄ ውድቅ ተደረገበት

አል አህሊ ከዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ ለሚያደርገው የፍፃሜ የመጀመርያ ጨዋታ ደጋፊዎቹ በብዛት እንዲገቡ ለግብፅ መንግስት ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ተደርጎበታል፡፡

በ2012 በፖርት ሰኢድ ስታድየም አል መስሪ ከ አልአህሊ ባደረጉት ጨዋታ በተከሰተው ብጥብጥ 72 የአል አህሊ ፣ 1 የአል መስሪ እና 1 የፀጥታ አስከባሪ መሞታቸው እና ከ500 ደጋፊዎች በላይ ጉዳት ማድረሱን ተከትሎ የግብፅ መንግስት በሁሉም የሃገሪቱ ስታድየሞች የሚደረጉ የክለብ ጨዋታዎች ያለ ተመልካች እንዲደረጉ ወስኖ እስካሁን ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ የግብፅ ክለቦች እና ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታዎች ላይም የቁጥር ገደብ ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡

በቅዳሜው የፍፃሜ የመጀመርያ ጨዋታ የአሌሳንድሪያው ቦርጅ አል አረብ ስታድየም ተመልካች የመያዝ አቅም ከ85ሺህ በላይ ሲሆን አል አህሊ ቢያንስ 70ሺህ ደጋፊዎቹ ስታድየም እንዲገቡ ጥያቄ ቢያቀርብም ከ50 ሺህ በላይ ተመልካች እንዳይገባ መንግስት አዟል፡፡

ይህን ጨዋታ ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ባምላክ ተሰማ በመሃል ዳኝነት እንዲመራው መመረጡ ይታወሳል፡፡

ቻን፡ አልጄርያ ግብፅን ተክታለች

የቻን አስተናጋጅ ሀገር የነበረችው ኬንያ አስተናጋጅነቷ ተነጥቆ ለሞሮኮ ከተሰጠ በኋላ በውድድሩ ላይ ኬንያን ተክቶ የሚካፈለውን ቡድን ካፍ መምረጡ ታውቋል፡፡ ግብፅ በውድድሩ ላይ እንድትሳተፍ ካፍ ጥያቄ ቢያቀርብም ግብፅ ለውድድሩ ብላ የሀገሯን ሊግ እንደማታቋርጥ በመግለጧ በምትኩ አልጄርያ በውድድሩ ላይ እንደምትሳተፍ ተነግሯል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *