ዳንኤል አጃዬ ወደ ጅማ አባ ጅፋር ተመለሰ

ሶስት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ካደረገ በኃላ ከሃገር ወጥቶ የነበረው ጋናዊው ግብ ጠባቂ ዳንኤል አጃዬ ከ2 ወራት ቆይታ በኋላ ወደ ጅማ አባ ጅፋር መመለሱ ታውቋል፡፡ በ2009 የፊፋ ዓለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ አሸናፊ የነበረው አጃዬ የፍርድ ቤት ጉዳይ አለብኝ በማለት ወደ ጋና ማቅናቱ ቢነገርም ተጫዋቹ ወደ አምስተርዳም ሆላንድ መሄዱ የሚታወስ ነው፡፡

የቀድሞ ሚዴአማ እና ሲምባ ግብ ጠባቂም ሌሊት ላይ አዲስ አበባ የደረሰ ሲሆን በቀጣይ ከሊጉ መሪ ደደቢት ጋር አባ ጅፋር ለሚያደርገው 13ኛ ሳምንት ጨዋታ ዝግጅት ክለቡን እንደሚቀላቀል ታውቋል፡፡ አጃዬ አባጅፋር ከሀዋሳ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ፋሲል ከተማ ጋር በቋሚነት ሲጀምር ሁለት ግቦችን በሶስት ጨዋታዎች አስተናግዷል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የጅማ አባ ጅፋር ስራ አስኪያጅ አቶ ኢሳያስ ጂራ አስተያየታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል፡፡ “ስለመመለሱ እርግጠኛ አይደለንም፡፡ ነገር ግን ሴት ልጁን የማሳደግ መብት በፍርድ ቤት ስለተወሰነለት እና በየወሩ የልጁን የትምህርት ሁኔታ የመከታተል ግዴታ ስላለበት ለተወሰነ ግዜ በየወሩ መጨረሻ ወደ አምስተርዳም የሚመላለስ ገልፆልናል፡፡” ብለዋል፡፡

በአጃዬ ምትክ ክለቡ ሌላ የውጪ ሃገር ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ጥረት ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም የአጃዬ ወደ ክለቡ ለመመለስ መስማማቱን ተክትሎ ሌላ ግብ ጠባቂ ለማምጣት ሲያደርገው የነበረውን ፍለጋ አቁሟል፡፡ ተጫዋቹ ከዚህ ቀደም ከጅማ አባ ጅፋርን ለቆ ከሄደ በኃላ ለፉቲጋና ድረ-ገፅ በሰጠው አስተያየት ከክለቡ ጋር ያለውን ውል ማፍረስ እንደሚፈልግ እና ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንደማይችል መግለፁ የሚታወቅ ነው፡፡

ከዚህ በፊት ከክለባቸው ጋር ያላቸውን ውል ሳያጠናቅቁ ወደ ሃገራቸው የሚያቀኑ ተጫዋቾች ሲመለሱ አለመታየታቸውን ተከትሎ የአጃዬም ጉዳይ ተመሳሳይ ቢመስልም ጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቹ እንዲመለስ የተሳካ ማግባባት ማድረግ ችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *