ቅዱስ ጊዮርጊስ አቤቱታ አቀረበ

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 30ኛ ሳምንት ጨዋታን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አቤቱታውን አቅርቧል።

ሙሉ ደብዳቤው ይህንን ይመስላል:-

ጉዳዩ ፡-    በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለሻምፒዮንነት የተደረጉ የ30ኛ ሣምንት ጨዋታዎችን አስመልክቶ የቀረበ አቤቱታ

ከቅርብ አመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ውስጥ የሚካሄዱ ጨዋታዎች የስፖርቱ ስነ ስርዓት የሚጠይቀውን መሠረታዊ ደንቦች የማያሟሉ፣ የእግር ኳስ ስፖርት ፅንሰ ሃሳብና መርሆዎች በገሃድ የሚጣሱባቸው መድረኮች ከመሆናቸው ባሻገር ከዕለት ወደ ዕለት ከዓመት ወደ ዓመት ችግሮቹ እየተባባሱና እየጨመሩ መሄዳቸውን መላው የስፖርት ቤተሰብ የሚገነዘበው ሃቅ ነው።

በተለይም ቡድኖች በውድድር ዘመን ማብቂያ አካባቢ ከሊጉ ላለመውረድ ሲሉ ጥያቄ የሚያስነሱ የርስ በርስ የመላቀቅና በግፍ ሌላ ቡድንን ከሊጉ የማስወጣት ጨዋታዎች ሲካሄዱ በፌዴፌሽኑ አንዳችም የእርምት ወይም በቀጣይነት ለወደፊት የመከላከያ መፍትሔ ርምጃዎች ለመውሰድ የተደረጉ አጥጋቢ ጥረቶች አልታዩም። ዘንድሮም ይሄው አጉል ልማድ ቀጥሎ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ሦስት የውድድር ዘመናት ከፍተኛ የሻምፒዮናው ተፎካካሪ የነበረውና በጨዋታ ከሁለት ግቦች በላይ አስተናግዶ የማያውቀው የአዳማ ከነማ ቡድን 5 ለ 0 በሆነ ውጤት በ30ኛው ሣምንት የሊጉ የመዝጊያ ጨዋታ ቀን በግብ ልዩነት ሻምፒዮን ለመሆን በሚጥረው የጅማ አባጅፋር ቡድን መሸነፉ ከላይ ከተጠቀሱት ኢስፖርታዊ አካሄዶች ጋር የሚደመር ነው።

ይልቁንም ዘንድሮ ጉዳዩን ወደባሰ ደረጃ ያሸጋገረው በዕለቱ ከጨዋታው በፊት ሁለቱም ቡድኖች ማለትም የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብና የጅማ አባጅፋር ክለብ የሻምፒዮንነቱን ዋንጫ የማንሳት እኩል ዕድል እንዳላቸው እየታወቀ፤ ቡድናችን በሚጫወትበት በአዲስ አበባ ስታዲየም አንዳችም የዋንጫ ወይም የሜዳልያ ሽልማት ዝግጅት በፌዴሬሽኑ አለመደረጉ በአመራሩ ጭምር ቡድናችንን ሳይጫወት ተሸናፊ ለማድረግ የታቀደ ነገር እንዳለ እንድንጠረጥር አድርጎናል።

ዘወትር በመልካም ስነ ምግባርና በዝማሬ ስታዲየሙን ሲያደምቁ የሚታወቁት የክለባችን ደጋፊዎች መካከል አንዳንዶቹ አነዚህ የተቀነባበሩ ሴራዎችን በገሃድ ሲካሄዱ በመመልከታቸው ስሜታቸው ተነክቶ በብሶትና በብስጭት ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች ውስጥ መሳተፋቸው ከስሜታዊነት የመነጨና ግልፅ ዘረፋ ሲካሄድ በሃላፊነት መፍትሔ ሰጪ አካል ካለመኖሩ የተነሳ እንደሆነ ምክንያቱን ለመረዳት አያዳግትም።

ስለሆነም የስፖርት ማህበራችን ፌዴሬሽኑ ይህንን ገሃድ የወጣ ፀረ እግርኳሳዊ ጉዳይ አስቸኳይና ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ፍትሕ እንዲሰጠን እየጠየቅን በዘልማድና በአሰራር እየተሳበበ የሚሰጠው የተለመደው የጨዋታው ኮሚሽነርና ዳኞች ሪፖርትን ተንተርሶ የተዛባ ውሳኔ ዓመቱን በሙሉ አቤቱታችንን ስናሰማ እንደከረምነው በሙስና፣ በአካባቢያዊነት ስሜት፣ በፍርሃትና በሌሎች ፀረ ስፖርታዊ አመለካከቶች ሰለባ የሆኑ የጨዋታ ሃላፊዎች የሚያቀርቧቸው ምስክርነቶች የችግሮቻችን ሌሎች ተጨማሪ ምንጮች እንጂ የመፍትሔ አካል እንዳልሆኑ ለማስገንዘብ እንወዳለን።

ከማክበር ሰላምታ ጋር