የሦስተኛ ሳምንት የእሁድ ጨዋታዎች | ቅድመ ዳሰሳ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ዛሬ ከሰዓት በኋላ ሽረ እና ሀዋሳ ላይ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይቀጥላል።


ሀዋሳ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

ዛሬ 9 ሰዓት ላይ በሀዋሳ ከተማ ስታድየም (ሰው ሰራሽ ሳር) የሚደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የደቡብ ክልል ቡድኖችን እርስ በእርስ የሚያገናኝ እንደመሆኑ ጠንካራ ፉክክር ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል። በክረምቱ የዝውውር መስኮት የተለያየ መልክ ያላቸው ግዜያቶች ያሳለፉት ሁለቱ ክለቦች የውድድር ዓመቱ መጀመርያ ላይ እንደመሆናቸው እንደ ሌሎቹ ክለቦች ሁሉ የስብስባቸውን ጥንካሬ የሚያሳዩበት እንደሚሆን ይጠበቃል። ሃዋሳ ከተማዎች በዝውውሩ ጥቂት ተሳትፎ ሲያረግ ወላይታ ድቻ በበኩሉ በርከት ያሉ ተጫዋቾች ማስፈረሙም የሚታወስ ነው።

በመጀመርያው ሳምንት ወልዋሎን በሰፊ ልዩነት አሸንፎ በሁለተኛው ሳምንት ወደ ጎንደር አቅንቶ ሽንፈት ገጥሞት የተመለሰው ሀዋሳ ከተማ በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ላለመጣል እና ከመሪዎቹ ላለማራቅ አጥቅቶ ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል። በመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ ወደ ሽረ ተጉዞ ከስሑል ሽረ ነጥብ ተጋርቶ የተመለሰው ወላይታ ድቻም በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሙሉ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ይፋለማል።

በጨዋታው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ በመስመር ለማጥቃት የሚሞክረው ሀዋሳ ከተማ ብዙ ግዜ ቦታቸው ለቀው ከማይሄዱት የወላይታ ድቻ የመስመር ተከላካዮች የሚጠብቀው ፈተና በጨዋታው ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት እና በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የተመሰረተው ወላይታ ድቻ በማጥቃቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸው የሃዋሳ የመስመር ተከላካዮች ትተውት የሚሄዱት ቦታ ተጠቅሞ በምን መልኩ ያጠቃል የሚለውም ሌላ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው። በአጠቃላይ ጨዋታው ከሌሎች የሜዳ ክፍሎች በበለጠ በመስመር ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ይገመታል።

በሀዋሳ በኩል አዳነ ግርማ ከፋሲል በነበረው ጨዋታ በተመለከተው ቀይ ካርድ ምክንያት  የማይሰለፍ ሲሆን እስራኤል እሸቱ ከሀገራዊ ግዴታው መልስ ለሀዋሳ ግልጋሎቱ ይሰጣል። በወላይታ ድቻ በኩል አሁንም ከጉዳት ማገገም ያልቻሉት ኃይማኖት ወርቁ ፣ እርቅይሁን ተስፋዬ ፣ ፀጋዬ ብርሀኑ ፣ ውብሸት ዓለማየሁ እና ውብሸት ክፍሌ ጉዳት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ሲሆኑ  እዮብ ዓለማየሁ ከጉዳት የሚመለስ ይሆናል።

ዳኛ

ይህን ጨዋታ ፌዴራል ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ 

ሀዋሳ ከተማ ( 4-3-3) 

ሶሆሆ ሜንሳህ 

አዲስዓለም ተስፋዬ – መሣይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ – ደስታ ዮሃንስ

ታፈሰ ሰለሞን – ምንተስኖት አበራ – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን

እስራኤል እሸቱ – ገብረ መስቀል ዱባለ – ኄኖክ ድልቢ

ወላይታ ድቻ

ታሪክ ጌትነት

እሸቱ መና – ተክሉ ታፈሰ – ዐወል አብደላ – ኄኖክ አርፊጮ

በረከት ወልዴ

ሐብታለም ታፈሰ – ፍፁም ተፈሪ – ቸርነት ጉግሳ – አብዱልሰመድ ዓሊ

ባዬ ገዛኸኝ


 

ስሑል ሽረ ከ አዳማ ከተማ

በዚህ ሳምንት ከሚደረጉት ጨዋታዎች አዝናኝ እና በርካታ ግቦች ይታዩበታል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ጨዋታ ሁለቱ አሰልጣኞች በሚከተሉት አጨዋወት ጥሩ ፍሰት ያለው ጨዋታ ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል። በቀዳሚ ሳምንት በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ ባደረጉት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አንድ ነጥብ ይዘው የወጡት ስሑል ሽረዎች በመጀመርያ ጨዋታቸው ነጥብ ማስመዝገባቸው ለዛሬው ጨዋታ የራስ መተማመናቸው ከፍ እንደሚያደርግላቸው ይጠበቃል። ነገር ግን ቡድኑ እንደሚፈጥራቸው የግብ እድሎች ግብ ማስቆጠሩ ላይ እንደተጠበቀው አለመሆኑ በቡድኑ ውስጥ እንደ ክፍተት የሚነሳ ነው።
በመጀመርያ ሳምንት በተደረገ ጨዋታ በሜዳቸው በቻምፒዮኑ ጅማ አባጅፋር የተረቱት አዳማ ከተማዎችም በውድድር ዓመቱ በተከታታይ ጨዋታ ነጥብ ጥሎ አስከፊ አጀማመር ላለማድረግ በሙሉ ኃይላቸው አጥቅተው እንደሚጫወቱ ይገመታል።

በጨዋታው የቀድሞ ክለባቸውን የሚገጥሙት ደሳለኝ ደባሽ እና ኄኖክ ካሳሁን እንዲሁም ሳሙኤል ተስፋዬ የመሃል ሜዳ ጥምረት በተሰጥኦ የተሻለ ከሆነው የአዳማ ከተማ የመሃል ክፍል የሚገጥማቸው ፈተና ይጠበቃል። ከዚ በተጨማሪ ፈጣኖቹ የአዳማ ከተማ አጥቂዎች የዘላለም በረከት እና ደሜጥሮስ ወልደስላሰ ጠንካራ ጥምረት ለመስበር ፈታኝ ይሆናል። 

በስሑል ሽረ በኩል ባለፈው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት ያልተሰለፈው ንስሃ ታፈሰ ከጉዳት ሲመለስ ሸዊት ዮሃንስም ከብሄራዊ ቡድን መልስ ቡድኑን ያገለግላል። በአዳማ በኩል በረከት ደስታ በጉዳት እንደማይሰለፍ ሲረጋገጥ ሌላው በጉዳት የነበረው ቡልቻ ሹራ ግን የመሰለፍ እድል እንዳለው ታውቋል።

ዳኛ 

ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ይህን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ሰንደይ ሮቲሚ

ሙሉጌታ ዓንዶም – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ -ዘላለም በረከት – ሸዊት ዮሐንስ

ደሳለኝ ደባሽ -ሄኖክ ካሳሁን 

ኢብራሂማ ፎፋና – ሳሙኤል ተስፋይ – ጅላሎ ሻፊ

ልደቱ ለማ

አዳማ ከተማ (4-3-3)

ጃኮ ፔንዜ

ሱሌማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ -ተስፋዬ በቀለ –  ሱሌይማን መሐመድ 

አዲስ ህንፃ – ኢስማኤል ሳንጋሪ – ከነዓን ማርክነህ

ዳዋ ሆቴሳ – ሙሉቀን ታሪኩ – ቡልቻ ሹራ