የአሰልጣኞች አስተያየት | ስሑል ሽረ 1-1 ሲዳማ ቡና

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ሽረ ላይ ስሑል ሽረ ከሲዳማ ቡና 1-1 ከተለያዩበት ጨዋታ በኃላ የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

” በዳኝነቱ አልተደሰትኩም ” ዳንኤል ፀሐዬ – ስሑል ሽረ

ስለጨዋታው …

” ጨዋታው ጥሩ ነበር። ሲዳማም ካየዋቸውም ቡድኖች ጥሩ ቡድን ነው። በተለይ ሲያጠቁ ጥሩ ናቸው። እኛ ደግሞ ዘጠኝ ተጫዋች ተጎድቶብናል ዛሬም ከቋሚው ውስጥ የሉም። ተጠባባቂ ወንበር ላይ ሁለት ሰው ብቻ ነው ያለው። ይህ መሆኑ ደግሞ ጎድቶናል። ዛሬ ራሱ ዝም ብዬ ነበር ተጠባባቂ ላይ ማልጠቀማቸውን አስቀምጬ የነበረው። ሁለት ብቻ ነበሩ ሊጠቅሙኝ የሚችሉት። ሦስት ሰው ስለሚቀየር ብዬ እንጂ ሌሎቹን የጨመርኩት ሜዳ ላይ ራሱ ሁለት እና አንድ ቀን ልምምድ የሰሩትን ነው ያሰለፍነው። ይህም አማራጭ ስሌለን ነው ልንጎዳ የቻልነው። በጨዋታው እንደተጀመረ ግን የግብ ዕድሎችን አግኝተን አምክነናል ሲዳማዎችም ቢሆኑ ያመከኗቸው አሉ። ጎል የሚገባብን በራሳችን ስህተት ነው። ከጊዮርጊስ እስከ አሁን የተከላካዮቻችንም ስህተቶች ናቸው ዋጋ ሚያስከፍሉን፡፡ የተከላካይ ስህተቶች በዝተውብናል፡፡ ”

ስለዳኝነቱ…

“ዳኝው የሚወስንብን ውሳኔ በሜዳችን የምንጫወት አይመስልም። በጣም ትልቅ ጫና ነበረው። ተጋጣሚያችንም ራሱ በዳኝነቱ አልተደሰተም። እኛም በተመሳሳይ ደስተኛ አይደለንም። በኛ ላይ የሚሰጣቸው ካርዶች ጥፋቶች በተለይ ማግኘት ያለብንን የጥፋት ውሳኔዎችንም አይሰጠንም ነበር”

” ሜዳው በፍፁም ኳስ መጫወት የማያስችል ነው ” ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

ስለጨዋታው…

” ጨዋታው ደስ አይልም። የዳኝነት በደል ነው ያየነው። እየመራን የተቆጠረብን ኳስ ከጨዋታ ውጭ የሆነ ነው። ቢያንስ ተጫዋቾቼ ላይ ለሚፈፀሙ ጥፋቶች ዳኛው ቀይ ካርድ ማሳየት ይገባው ነበር። በዚህም በጣም አዝኛለሁ። አዲስ ግደይ ላይ በተደጋጋሚ ጥፋት ሲፈፀምበት ከቢጫ ካርድ ውጭ አንዴ እንኳን ቀይ ካርድ ማሳየት አልቻለም። የሚያሳፍር ዳኝነት ነው ያየሁት። እንኳን እኛ የሽረ ደጋፊዎች እንኳን ዳኛውን ሲቃወሙ ነበር። ለሽረ ደጋፊዎች ትልቅ አክብሮትም አለኝ። የገባብን ኳስ ከጨዋታ ውጭ የሆነ ስለሆነ ዋጋ አስከፍሎናል። ”

ስለሜዳው…

” ሜዳው በፍፁም ኳስ መጫወት የማይቻልበት ነው። በዚህ ሜዳ ኳስን እጫወታለሁ ማለት ለሊጋችንም የሚመጥን አይደለም። “