የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 2-0 ደደቢት

በ10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ባህር ዳር ላይ ባህር ዳር ከተማ ደደቢትን 2ለ0 አሸንፏል። ከጨዋታው በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ስለ ጨዋታው የሚከተለውን ብለዋል

“በሙሉ 90 ደቂቃው አጥቅተን በመጫወታችን አሸንፈን ወጥተናል።” የባህር ዳር ከተማ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው

ስለ ሁለቱ ክልል ክለቦች እርስ በእርስ ጨዋታ

“ከእግር ኳሱ በዘለለ የነበረው የሁለቱ ክልሎች መጥፎ ነገር ተቀርፎ በየራሳቸው ሜዳ መጫወት መጀመራቸው ከውጤቱ ጉን ለጎን አስደስቶኛል። የባህር ዳር ህዝብም እንግዳ ተቀባይነቱን ያሳየበት ተጋጣሚ ቡድንም በስነስርዓት ተጫውቶ በሰላም የሄደበት በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ።”

ስለ ጨዋታው እንቅስቃሴ

“እንደታየው በሙሉ 90 ደቂቃው አጥቅተን ሁለት ጎሎችን አስቆጥረን አሸንፈናል። ነገር ግን ብዙ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ፈጥረን አምክነናል። ቡድኔ አንዳንድ ነገር እንደሚቀረው ባውቅም ወደ ፊት ያሉብንን ክፍተቶች አስተካክለን በየጨዋታው የተሻለ ሆኖ ለመቅረብ እንሞክራለን።”

በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ኋላ አፈግፍገው ስለተጫወቱበት ጉዳይ

“ጎሎችን ካስቆጠርን በኋላ ወደ ኋላ አፈግፍገን ለመጫወት የሞከርነው ጉልበታችንን ለመቆጠብ ነው። ሀሙስ ወደ መቐለ ተጉዘን ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ጋር ጨዋታ አለብን። ስለዚህ አቅማችንን መሰብሰብ እንዳለብን በማመናችን ነው እንደ አጀማመራችን ያልቀጠልነው።”

ስለ ቡድናቸው

“እኔን ደስ ያላሉኝ ነገሮች አሉ ወደ ፊት ይፋ የማደርጋቸው። እኔን የወከለኝ የባህር ዳር ህዝብ ነው። ህዝቡ የሚፈልገውን ነገር ደግሞ በትክክል ነው መስራት የምፈልገው። በትክክል መስራት የማልችል ከሆነ ደግሞ የቡድኑን ውጤት ማበላሸት ስለማልፈልግ ራሴን አገላለው። በቡድኑ ማኔጅመንት ደስተኛ ነኝ ነገር ግን ወስጣችን ያሉ ነገሮች ስላሉ ከቡድኑ ማኔጅመንት ጋር ተነጋግረን ችግሮችን ለመፍታት እንሞክራለን።”

ስለ ተጋጣሚያቸው

“ደደቢቶች ጥሩ ናቸው። ወደ ፊት ለመሄድ ይፈልጋሉ ነገር ግን እኛ በሜዳችንም እንደመጫወታችን እና ጠንካራ እንደመሆናችን ብልጫ ወስደን አሸንፈናቸው ወጥተናል።”

ስለ ቡድኑ የአጥቂ መስመር ስል አለመሆን

“እግር ኳስ ዋናው ቁምነገሩ ጎል ጋር የመድረሱ ጉዳይ ነው። ተጨዋቾቼ ጎል ጋር ደርሰው የፈለጉትን ያድርጉ፤ ያንን ደግሞ እኛ እናርማለን። ዛሬም በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል እንደርስ ነበር፤ ነገር ግን ኳሶችን አምክነናል። ወደ ፊት ግን ይህንን ችግር እናስተካክላለን።”


“በሰራናቸው ተመሳሳይ ስህተቶች ጎሎች ተቆጥረውብን ተሸንፈናል” የደደቢት አሰልጣኝ ኤሊያስ ኢብራሂም

ስለ ሁለቱ ክልል ክለቦች እርስ በእርስ ጨዋታ

“በመጀመሪያ ደረጃ ሁለቱም ክልሎች ተስማምተው ጨዋታዎችን በየሜዳችን ማድረግ ስለጀመርን በደደቢት እግር ኳስ ክለብ ስም በጣም ማመስገን እፈልጋለው።”

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታው ሁለት መልክ ነበረው። ከእረፍት በፊት በተለይ በመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች ተጋጣሚያችን ተጭኖን ነበረ የተጫወተው ቢሆንም ግን ሲሰነዘሩብን የነበሩትን ጫናዎች ተቋቁመን ወደ ራሳችን ቅኝት ገብተን ለመጫወት ሞክረናል። ነገር ግን በአጋጣሚ ራሳችን ላይ ጎል አስቆጥረናል። ከእረፍት በኋላ ደግሞ በተለይ መሃል ሜዳውን ተቆጣጥረን በ15 ደቂቃዎች ውስጥ ጎሎችን ለማስቆጠር ነበር የሞከርነው። ነገር ግን ተመሳሳይ ስህተት ፈፅመን ጎል ተቆጥሮብናል።”

በሁለተኛው አጋማሽ ስለወሰዱት እርምጃ

“ከእረፍት በፊት እንደታየው ብልጫ ተወስዶብናል። ይህ ደግሞ የሆነው አንደኛ በሜዳውም ስፋት ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ተጋጣሚያችን ጥቃቶችን ሲሰነዝርብን የነበረው በመስመር በኩል በመሆኑ ነው። ስለዚህ ይህንን ነገር ለመከላከል መሀል ሜዳ ላይ ለውጦችን አድርገን ጥሩ ተንቀሳቅሰናል።”

ስለቡድኑ የአጥቂ መስመር ድክመት

“ከፊት አንድ አጥቂ ነበር አድርገን የተጫወትነው። የነበረን የአጥቂ ክፍል ደግሞ ከልምድ እና ከተለያዩ ምክንያቶች ድክመቶች ነበሩበት፤ ቢሆንም ግን አስበን የነበረው የግብ እድሎችን ከአማካይ ተጨዋቾቻችን ለማግኘት ነበር። በአጠቃላይ ግን ሽግግሮች ላይ ክፍተቶች ስለነበሩብን ጎሎችን ማስቆጠር አልቻልንም።”

ስለ ተደረገላቸው አቀባበል እና ስታዲየሙ ውስጥ ስለነበረው ድጋፍ አሰጣጥ

“ከገባንበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን የተደረገልን ነገር ጥሩ ነው። በዚህ አጋጣሚ ለባህር ዳር ህዝብ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለው። በሜዳም ላይ የነበረው ድጋፍ ጥሩ ነበር። ደጋፊው የራሱን ቡድን እየደገፈ ተቃራኒ ቡድኑን እያበረታታ ስለነበር ጥሩ ነው፤ በዚሁ ይቀጥል።”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *