የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 0-0 አዳማ ከተማ

ጅማ ላይ የተከናወነው የጅማ አባ ጅፋር እና አዳማ ከተማ ጨዋታ ያለ ጎል ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች የሰጡትን አስተያየት እነሆ።

የሱፍ ዓሊ – ጅማ አባጅፋር


የዛሬ የቡድኑ ድክመት

ለዚህ ጨዋታ በሁለት አጥቂዎች ለመጫወት (በ4-4-2 አሰላለፍ) ነበር ስንዘጋጅ የቆየነው። ኦኪኪም ሶስት ልምምዶች ላይ አብሮ ነበር ለዛሬው ጨዋታ ባለመድረሱ እቅዳችንን በመጀመሪያው ዙር ስንጠቀምበት ወደነበረው ወደ 4-3-3 ለመቀየር ተገደናል፡፡

ኦኪኪ የወረቀት ስራዎች ፌደሬሽን እንዳልጨረሰ እየታወቀ የቡድኑ አካል አድርጎ ቡድኑ በሱ ላይ ሰለመመስረቱ

በልምምድ ወቅት በሙሉ ቡድኑ እንደሚኖር ታሳቢ ተደርጎ ነበር ሲሰራ የቆየው። እዛ ሄዶ ነው ሀሳቡን ቀይሮ ቀሪ ገንዘብ ካልተከፈለኝ አልፈርምም ያለው።

በጊዜ ያገኙትን የቁጥር ብልጫ አለመጠቀምና ተቀይረው ስለገቡ ተጫዋቾች

ሄኖክና አክሊሉ የመከላከል ባህሪ ቢኖራቸውም ማጥቃቱም ላይ እንጠቀማቸዋለን። ሄኖክን ብዙውን ጊዜ ማጥቃት ላይ ነው የምንጠቀመው። ለዛም ነው በመስዑድ የቀየርነው። ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በሶስት ተከላካዮች ለመጫወት ጥረት አድርገናል።

ሲሳይ አብርሃ – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው

በመጀመሪያ ይህን ሁሉ ኪሎሜትሮችን አቋርጠን ስንመጣ ለማሸነፍ ነበር። በጨዋታ ላይ መሸነፍም ሆነ አቻ መውጣት ለውጥ የለውም። ከጨዋታ በፊትም ተነጋግረን የነበረው የዛሬውን ጫዋታ አሸንፈን አራተኛ ደረጃን ለመያዝ ነበር። ሆኖም በጊዜ በቀይ ካርድ ብዙዓየሁ መውጣቱ እቅዳችንን አልተሳካም፡፡

የበረከት እና ከንዓን ያለመኖር ተፅዕኖ

ሜዳ ላይ በነበሩት ተጫዋቾች የነበረው ነገር ጥሩ ነው። እነዚህም ተጫዋቾች ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል፤ ተደጋጋሚ እድሎችንም ፈጥረን አልተጠቀምንባቸውም። ሀገራዊ ግዴታ ስለሄዱ ግዴታችን ነው። ሮበርት ኦዶንካራም ኡጋንዳ ለብሄራዊ ቡድን ተጠርቶ ሄዷል። አትሂዱ ብለን መከልከል አንችልም። እነሱን ተክተው የተሰለፉት ተጫዋቾችም ጥሩ ተጫውተዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *