ሪፖርት | ጅማ አባ ጅፋር ከሜዳው ውጪ መከላከያን ረምርሟል

አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ጅማ አባ ጅፋርን ያስተናገደው መከላከያ 4ለ0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።
በሁለተኛው ዙር ጅማሮ በደቡብ ፖሊስ ሽንፈት ያስተናገደው መከላከያ በዛሬው ስብስቡ ውስጥ በአዲሱ ተስፋዬ ፣ ታፈሰ ሰረካ ፣ በኃይሉ ግርማ እና ምንይሉ ወንድሙ ቦታ ምንተስኖት ከበደ ፣ ሙሉቀን ደሳለኝ ፣ አመኑኤል ተሾመ እና ዳዊት ማሞን ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ አምጥቷል። ጅማ አባ ጅፋሮች ግን ከአዳማ ጋር ያለግብ ከተለያዩበት ጨዋታ ንጋቱ ገብረስላሴን በአክሊሉ ዋለልኝ ብቻ በመቀየር ጨዋታውን ጀምረዋል።

የግብ ሙከራዎች በብዛት ያልታዩበት የመጀመሪያ አጋማሽ በጅማዎች ጫና የጀመረ ነበር። በፈጣን ጥቃት ወደ መከላከያ ሳጥን መቅረብ የቻሉት አባ ጅፋሮች ከረጅም ርቀት ያገኙትን ቅጣት ምት ማማዱ ሲዲቤ በቀጥታ መትቶ አቤል ማሞ ነበር ያወጣበት። ቀስ በቀስ መረጋጋት የቻሉት መከላከያዎች በቀጣዮቹ በርካታ ደቂቃዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ማሳካት ቢችሉም በጅማ አጋማሽ የቆዩባቸው ደቂቃዎች ግን የመጨረሻ የግብ ዕድል የፈጠሩባቸው አልነበሩም። እንግዶቹ ጅማዎችም አልፎ አልፎ መሀል ሜዳ ላይ ከሚያስጥሏቸው ኳሶች መነሻነት ወደ ጦሩ የግብ ክልል ይቀርቡ ነበር። ነገር ግን ሁለቱም በኩል ከሳጥን ውጪ ያደርጓቸው የነበሩት ሙከራዎች በተከላካዮች የሚደረቡ ነበሩ።

የፊት አጥቂያቸው ማማዱ ሲዲቤ ወደ አማካይ ክፍሉ በመቅረብ በሚሰጠው እገዛ የባለሜዳዎቹን የኳስ ቁጥጥር ያለችግር ይቆጣጠሩ የነበሩት ጅማዎች ከ30ኛው ደቂቃ በኋላ ተደጋጋሚ ጥቃት ፈጥረዋል። 32ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለው ሳጥን ውስጥ ከይሁን ተቀብሎ አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት በአቤል ተመልሶበት ወደ ውጪ የወጣበት ሲሆን ወደ ውጪ የወጣውን ኳስ ተከትሎ የማዕዘን ምትም ያገኙት ጅማዎች በአክሊሉ ዋለልኝ የግንባር ኳስ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። ቡድኑ የፈጠረው ጫና ግን 38ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቷል። ከቀኝ መስመር የተላከውን ረጅም ኳስ ማማዱ ሲዲቤ እና አበበ ጥላሁን በግንባራቸው ተሻምተው ሲወርድ ሳጥኑ መግቢያ ላይ የነበረው መስዑድ በቀጥታ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሯል። ባለሜዳዎቹ በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ የሚሰሯቸው የቅብብል ስህተቶች እንደተለመደው ዋጋ ሊያስከሏቸው ሲቃረቡም ነበር። በተለይም 45ኛው ደቂቃ ላይ ይሁን እንዳሻው መሬት ለመሬት የሰነጠቀለትን ኳስ አስቻለው ግርማ ከአቤል ጋር ነፃ ሆኖ ተገናኝቶ አመከነው እንጂ የቻምፒዮኖቹ መሪነት ወደ ሁለት የመስፋት ዕድል ነበረው።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ሳሙኤል ታዬን በአቅሌሲያስ ግርማ ቀይረው በማስወጣት የአማካይ ቁጥራቸውን ቀንሰው በሁለት አጥቂዎች ለመቀጠል ወስነዋል። አቅሌሲያስ 52ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት ከተመለሰ ኳስ ባደረገው ሙከራም መከላከያ የመጀመሪያውን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራም አድርጓል። ከዚህ ሙከራ ውጪ መከላከያዎች ኳስ ከማንሸራሸር ባለፍ በሌሎች ሙከራዎች ለዳንኤል አጄዬ ፈተና ሲሆኑ ግን አልተስተዋለም። ይልቁኑም በቶሎ የሚቆራረጡት ቅብብሎቻቸው ራሳቸውን ለመልሶ መጠቃት አሳልፈው እንዲሰጡ ምክንያት ሆነዋቸዋል። በዚህ መሰረትም 65ኛው ደቂቃ ላይ በጦሩ ሳጥን ውስጥ የደረሱት ጅማዎች ማማዱ ሲዲቤ መትቶት ተከላካዮች የተደረቡትን ኳስ በዐወት ገብረሚካኤል አማካይነት ወደ ግብነት ቀይረው መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል።

በአመዛኙ ከኳስ ጀርባ መሆንን ምርጫቸው ያደረጉት ጅማዎች በድንገት በሚሰነዝሯቸው ጥቃቶች ወደ ግብ በሚደርሱባቸው ጊዜያት ይበልጥ አስፈሪ ሆነው ታይተዋል። ይህ አካሄዳቸውም በተጋጣሚያቸው ላይ ጨዋታውን ይበልጥ ለማክበድ ረድቷቸዋል።
74ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ማሞ ተጎድቶ በወጣበት እና መከላከያዎች ቅያሪ ባላደረጉበት ሰዓት የቁጥር ብልጫን ያገኙት ጅማዎች በግራ መስመር በመግባት ወደ መሀል ያሻሙትን ኳስ ማማዱ ሲዲቤ በአቤል አናት ላይ በመላክ ጥሩ ጨራሽነቱን ያሳይች ግብ አስቆጥሯል። ባለሜዳዎቹ መከላከያዎች በተመሳሳይ መንገድ በአጫጭር ቅብብሎች ወደ ግብ ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት 72ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን በግራ በኩል ገብቶ ካደረገው ሙከራ በኋላ ሌላ ዕድል ሳይፈጥሩ ጨዋታውን አጠናቀዋል። በጅማ በኩል ግን 88ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ብሩክ ገብረዓብ ያመቻቸለትን ኳስ መስዑድ ከሳጥን ውስጥ ከፍ አድርጎ በአቤል መረብ ላይ ሌላ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በ4-0 ውጤት ተጠናቋል።

በውጤቱም አባ ጅፋር አራት ደረጃዎችን አሻሽሎ ወደ ስድስተኝነት ከፍ ሲል መከላከያ ወደ 13ኛ ደረጃ ዝቅ ለማለት ተገዷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *