“ዋንጫ የማንሳት ዕድሉ አለን ” ሐብታሙ ገዛኸኝ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተመለከትናቸው ካሉ ወጣት እና ፈጣን የመስመር ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፤ የሲዳማ ቡናው ሐብታሙ ገዛኸኝ። በተለይ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በክለቡ ውጤታማ ጉዞ ውስጥ ስማቸው ከፊት ከሚጠሩ ተጫዋቾች ውስጥ የሚካተተው ሐብታሙ በሊጉ 22 ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈ ሲሆን በ2 አጋጣሚዎች ብቻ ተቀይሮ ወጥቷል። በሜዳ ላይ በቆየባቸው 1978 ደቂቃዎችም 7 ጎሎችን አስቆጥሮ 4 ጎል የሆኑ ኳሶችን ለአጋሮቹ አመቻችቷል።

በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ በመልካም የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ታግዞ ግቦችን በማስቆጠር እና የቡድኑን የፊት መስመር አስፈሪ በማድረግ ክለቡን በዋንጫ ተፎካካሪ ዝርዝር ውስጥ እንዲቆይ የድርሻውን እየተወጣ የሚገኘው የቀድሞው የደቡብ ፖሊስ አጥቂ ዘንድሮ እያሳየ ስላለው አቋም እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ትውልድህ እና የእግር ኳስ አጀማመርህ ?

ተወልጄ ያደኩት በቤንች ማጂ ዞን ቴፒ ከተማ ውስጥ ነው። እግር ኳስን የጀመርኩትም ከሰፈር ነው። በዞን ውድድር ላይ ኮከብ ሆኜ ጨርሼ ቤንች ማጂን በመወከል ሀዋሳ ለውድድር ሄድኩኝ። ሆኖም በነበረኝ ቆይታ ብዙም ስኬታማ አልነበርኩም። ከዛ ተመልሼም በቀጣይ ዓመት እንደዚሁ ተመሳሳይ ውድድር መጣና ተጫወትኩ ፤ በወቅቱ ውድድሩ ሆሳዕና ላይ ነበር የተካሄደው። እዚህ ውድድር ላይ ግን በተሻለ ብቃት የኮከብ ግብ አግቢነት ሽልማትን አገኘሁ። በዚህም ለክልል እመረጣለሁ ብዬ አስቤ የነበረ ቢሆንም ሳልመረጥ በመቅረቴ ተስፋ ቆርጬ ተመለስኩኝ። ነገር ግን እንቅስቃሴዬን የተመለከተው ወደ ብሔራዊ ሊግ ለመግባት የሚጫወተው ‘ምዕራፍ አዘርነት’ ወይም ‘አስሚድ’ የተባለው ክለብ የደቡብ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ላይ እንድጫወትላቸው ጠሩኝ። ጥያቄውን በመቀበልም ለውድድር ወደ ወላይታ ከተማ በማምራት ሶዶ በነበረው የክለቦች ሻምፒዮና ላይ ዘጠኝ ግቦችን አስቆጥሬ የኮከብ ግብ አግቢነትን ክብር አገኘሁ። በዛ ውድድር ላይ በወቅቱ የደቡብ ፖሊስ ክለብ የበላይ ጠባቂ የነበረው ኮሚሽነር ፍሰሀ በመዝጊያው ቀን ላይ በደቡብ ፖሊስ እንድጫወት አናገረኝ። በጊዜው 2007 ላይ ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት የማጠቃለያ ውድድር ነበረበት። ለዛም ለጊዜው ቢጫ ቴሴራ ይሰራልህ ፤ ቀጣይ ስትመጣ ወደ አረንጓዴ ይለወጥልህ እና ነው የምትፈርመው አሉኝ። ወደ ድሬዳዋም አብርያቸው በመሄድ ሁለት ጨዋታዎች ላይ በደቡብ ፖሊስ መለያ መጫወት ቻልኩኝ። አንድ ግብ የሆነ ኳስን አቀብዬም አንድ ግብ አስቆጠርኩኝ። ውድድሩ ሲያልቅ ክረምት ወደ ቤተሰብ ተመልሼ ሄድኩኝ እና በ2008 ተመልሼ መጥቼ በደቡብ ፖሊስ የሁለት ዓመት ቆይታን ለማድረግ ፈረምኩኝ። በመጀመሪያው ዓመቴ ግን ብዙም አልነበርኩም ፤ ያው ልምድም ስላልነበረኝ አዲስም ስለሆነብኝ ጥሩ ጊዜ አልነበረኝም። ሁለተኛው ዓመት ላይ ግን ጥሩ ነገርን ከክለቡ ጋር ካሳለፍኩኝ በኃላ 2010 ላይ ሲዳማ ቡናን ለመቀላቀል በቃው።

በሲዳማ ቡና የመጀመሪያ ዓመት ቀዝቀዝ ያሉ ጊዜያትን ነበር ያሳለፍከው ፤ ዘንድሮ ግን ተሽለህ መጥተሀል። የእስካሁኑ ቆይታህ እንዴት ነው ?

ፕሪምየር ሊግ በጣም ይከብዳል። ከታች ስትመጣ የመጀመሪያው ዓመት እንደ አዲስ ነው የሚሆንብህ። ጥሩ ነገር ለማሳየት ልምድ እስኪኖርህ ድረስ ይከብዳል። እኔም ልምድ እያገኘሁ ስመጣ በተለይ አምና ከግማሽ በኃላ ሲዳማ ቡና ላለመውረድ እየተጫወተ የነበረ ቢሆንም የመሰለፍ ዕድል እያገኘው ነበር። ጥሩ ነገር ሰርቼም የደሞዝ ማስተካከያም ተደርጎልኛል። ሁለተኛው ዙር ላይ ካሳየሁት እንቅስቃሴ አንፃር የመጀመሪያ ዓመት ቆይታዬ ትምህርት የወሰድኩበት በመሆኑም ፕሪምየር ሊጉ እንደሚቀለኝ ማሰብ ጀመሪያለው። ‘አንተ ጠንክረህ ከሰራህ ምንም ነገር ማድረግ ትችላለህ’ የሚል ሀሳብን ይዤ ጠንክሬ መስራት ቀጥዬ አሁን ጥሩ ነገርን ማሳየት ጀምሪያለው።

ዘንድሮ ሲዳማ ለዋንጫ እየተፎካከረ ነው። አንተም በተለይ በሁለተኛው ዙር በተሻለ አቋም ላይ ተገኝተህ ከአዲስ ጋር ጎሎችን እያስቆጠርክ ነው። የዚህን ዓመት እንቅስቃሴህን እንዴት አየኸው ?

ከአሰልጣኜ ጋር እናወራለን። ‘አንደኛው ዙር ላይ ለየት ያለ እንቅስቃሴን ማድረግ አለብህ’ ይለኝ ነበር። ከዛ በኋላም ‘አንደኛው ዙር ላይ በነበረህ ነገር አልተከፋሁም ፤ ሁለተኛው ዙር ላይም በአንተ ላይ ዕምነቴን ጥያለሁ ፤ አንተ ጥሩ ከሆንክ እናሸንፋለን’ ብሎኛል። አሰልጣኝ ዘርዓይ ይህን ሲለኝ ጠንክሬ መስራት እንዳለብኝ ነው ያመንኩት። አዲስ ግደይም ጥሩ ነው ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥሩ ከሚባሉ የመስመር አጥቂዎች ውስጥ አንዱ እሱ ነው። በአብዛኛው ቡድናችን በአንደኛው ዙር የማጥቃት እንቅስቃሴው ወደ ግራ ሚያያደላ ነበር። ሁለተኛው ዙር ላይ ግን ተነጋግረን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ በእኔም በአዲስም በኩል ለመጫወት ነው የሞከርነው። ወደ እሱ ብቻ ሲሆን ጫናዎች በሱ ላይ ብቻ ይሆናሉ ፤ ያም ያደክመዋል። በመሆኑም በተቻለን አቅም ሚዛኑን እየጠበቅን በሁለታችንም በኩል እየተጫወትን ነው።

በደቡብ ፖሊስ በፊት አጥቂነት ነበር ተሰልፈህ ስትጫወት የነበረው። ወደ ሲዳማ ቡና መጥተህ ወደ መስመር አጥቂነት ተለውጠህ እየተጫወትክ ስኬታማም እየሆንክ ነው። ይህ ቦታ ላንተ ተመራጭ ነው ማለት ይቻላል ?

ከልጅነቴ ኳስ ስጀምር አጥቂ ሆኜ ነው። ፖሊስም እያለሁ አጥቂ ሆኜ ነው የጨረስኩት፤ ሰው ሲጠፋ ግን ግማሽ አጥቂ ግማሽ የመስመር ተጫዋችም ነበርኩ። ትክክለኛው ቦታዬም የመስመር አጥቂነት ነው። ሲዳማም ስመጣ በተመሳሳይ ሰው ከተጎዳ አጥቂ ሆኜ እጫወታለሁ። ለኔ የሚመቸኝ ግን የመስመር አጥቂነቱ ነው።

ሲዳማ ቡና ለዋንጫ ተፎካካሪ ከሆኑ ክለቦች አንዱ ነው። የዘንድሮው የዋንጫ ጉዟችሁን እንዴት ታየዋለህ ?

ትንሽ ዘንድሮ ሊጉ ከበድ ይላል። ሆኖም አሁንም ለዋንጫ እየተፎካከሩ ያሉት ሌሎች ክለቦች ቀጣይ ጨዋታዎቻቸው ከሜዳ ውጪ ስለሆኑ ትንሽ ሊከብዳቸው ይችላል። በአንፃሩ ከነሱ አንፃር የኛን ስታይ ቀለል ይላል። እኛ አሁን የነሱን ነጥብ መጣል አለመጣል አናይም። ከፊት ያሉ ጨዋታዎችን እያሸነፍን የሚመጣውን ውጤት በፀጋ መቀበል ነው የሚኖርብን። ግን ዋንጫ የማንሳት ዕድሉ አለን። ይህን ያልኩት ከሜዳ ውጪ ብዙ ጨዋታ ስለሌለንም ነው። ላለመውረድ የሚጫወተውን ደደቢት እና መከላከያን ነው የምንገጥመው። ሌሎች ጨዋታዎች በሜዳችን የምናደርጋቸው ናቸው። እናም ዋንጫውን እናነሳለን የሚል ግምት ነው ያለኝ ፡፡

ከዕለት ወደ ዕለት በሜዳ ላይ የተሻልክ እየሆንክ መጥተሀል ግቦችንም ከማስቆጠር ባለፈ ለቡድንህ ስኬታማ ጊዜ አስተዋፅኦህ ከፍ እያለ ነው። እና ከአሁን በኃላስ ከአንተ ምን ይጠበቃል ? ዕቅድህስ ምን ይሆን ?

አቅሜን እያጎለበትኩኝ ከእኔ የሚጠበቁ ስራዎችን እየሰራሁ ከዚህ በላይ መጫወትን እፈልጋለሁ። በቅድሚያ ዕድሉን ካገኘሁ ወደ ውጪ ወጥቶ የመጫወት ዓላማ አለኝ። በሊጉ ላይ ግን ጥሩ ከሚባሉ ተጫዋቾች ውስጥ ራሴን አካትቼ መገኘት ነው የምፈልገው። የትም ክለብ ውስጥ ገብቼ በመጫወት ጥሩ ነገርን ሰርቼ ስሜን እንደ አዳነ ግርማ እና ጌታነህ ከበደ ከፍ ለማድረግ ነው የምሰራው። ብሔራዊ ቡድናችንንም ለመጥቀም ጠንክሬ ሰራለሁ ፤ ለክለቤም ይህንኑ አደርጋለሁ። የቡድን ጓደኞቼም ይህን እንዳሳካ እንደሚረዱኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

በቅርቡ በወጣት ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካተህ ተጫውተሀል ፤ ጥሩም ነገር ነበረህ። በቀጣይ በዋናው ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተጠርቶ ለመጫወት ያለህ ጉጉት ምን ይመስላል ?

(ሳቅ) ፍላጎቱ አለኝ። ባለፈው ለወጣት ብሔራዊ ቡድን ተጠርቼ ጥሩ መጫወት ችያለሁ። ‘ይሄን ያሳየውትን ነገር ለምን ወደ ላይኛው አላመጣሁም ?’ የሚል ጥያቄ በራሴ አድሮብኛል። አሰልጣኝ አብርሀምም ጥሩ ነው። አንድ ጊዜ ጠርቶኝ እንደውም ‘ወደ ላይኛው ብሔራዊ ቡድን ተካተህ ትሰራለህ’ ብሎኝ ነበር። ‘እጠራሀለው የምታሳየው ነገር ጥሩ ነው ፤ አንተ ተተኪ ነህ’ ይለኝ ነበር። ‘ጠንክራችሁ ስሩ’ እያለ ጥሩ ነገር የነበረንን ተጫዋቾች ያበረታታንም ነበር። ‘የምጠራችሁ ጊዜም ቅርብ ነው’ ብሎናል። ያን ታሳቢ በማድረግም ጠንክሬ እየሰራሁ ነው ፡፡

አንድ ታዳጊ ከጅማሮው አርዓያ የሚያደርገው ተጫዋች ይኖራል፤ አንተም ‘እሱን እያየው ነው ያደኩት’ የምትለው ተጫዋች ይኖራል ? በፊት እና አሁንም የምታደንቀው ተጫዋች ማንን ነው ?

በፊት የማደንቀው ጌታነህ እና አዳነን ነው። በአጥቂ ቦታ ላይ እጫወትም ስለነበር ጌታነህ ከበደ ምሳሌዬ ነው። በፊት በኳስ እዚህ ለመድረሴ ትልቁን ቦታ ሚወስደው ታላቅ ወንድሜ ባዬ ገዛኸኝ ነው። በዚህ አጋጣሚ ላመሰግነው እወዳለሁ። (አሁን በወላይታ ድቻ የሚገኘው ባዬ ዘንድሮ ከሐብታሙ ጋር ዕኩል 7 የሊግ ጎሎች አስቆጥሯል) ለጌታነህ ከበደ እና አዳነ ግርማ ደግሞ የተለየ ቦታ አለኝ። ከአሁን ተጫዋቾች ደግሞ ከበድ ያለ ኳስን ሲጫወት ደስ የሚለኝ የመቐለው አማኑኤል ገብረሚካኤል ነው፤ እንቅስቃሴውም ያስደስተኛል፡፡

በመጨረሻ…

በመጀመሪያ ቤተሰቦቼን ማመስገን እፈለጋለሁ። እንደዚህ በችግር ሰዓት ሰው ኳስን ወዶ ትምህርቱን በሚተውበት ጊዜ እነሱ ግን ኳሱንም ትምህርቱንም አንድ ላይ እንዳስኬድ ረድተውኛል። ሲቀጥል የማመሰግነው ታላቅ ወንድሜ ባዬ ገዛኸኝን ነው። ሌላው ደግሞ የአሁኑ የነቀምት ከተማ አሰልጣኝ ቾምቤ ገብረህይወትን ማመስገን እፈልጋለሁ። ፖሊስ በነበርኩበት ጊዜ ከጎኔ ሆኖ እንደ አባት ነበር ሲመክረኝ የነበረው። ‘ትልቅ ቦታ ትደርሳለህ አሰልጣኝ የሚልህን ስማ’ እያለ ብዙ ነገር ሲለኝ የነበረው ቾምቤን ላመሰግነው እወዳለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡