ሪፖርት| ደቡብ ፖሊስ ከመመራት ተነስቶ ሀዋሳን በማሸነፍ ላለመውረድ በሚያደርገው ትንቅንቅ ቀጥሏል

የአንድ ከተማ ክለቦችን ያገናኘው የ27ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ደቡብ ፖሊስ ሀዋሳ ከተማን አስተናግዶ ከፍፁም ከጨዋታ ብልጫ ጋር 3-2 አሸንፏል።

ደቡብ ፖሊሶች በሲዳማ ቡና ከተረቱበት ጨዋታ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ መክብብ ደገፉ፣ ዘነበ ከድር እና ዮናስ በርታን በማሳረፍ ሀብቴ ከድር፣ አበባው ቡጣቆ እና ኤርሚያስ በላይን በመጀመርያ አሰላለፍ አስገብተዋል። ሀዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ሶሆሆ ሜንሳህ፣ ያኦ ኦሊቨር፣ ምንተስኖት አበራ እና እስራኤል እሸቱን በማስወጣት ተክለማርያም ሻንቆ፣ መሳይ ጳውሎስ፣ አክሊሉ ተፈራ እና ሄኖክ ደልቢን አስገብተዋል።


በሁለቱም በኩል ማራኪ እና ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል የሚደርስ እንቅስቃሴን ባስመለከትን የመጀመሪያው አጋማሽ በደቡብ ፖሊስ በኩል በተለይ ብሩክ ኤልያስ በቀኝ የማጥቃት መስመር ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮችን ሲያስጨንቅ ተስተውሏል። ሀዋሳዎች በበኩላቸው የፊት አጥቂያቸው መስፍን ታፈሰ ላይ በማነጣጠር እና በቀኝ መስመር በኩል በማጋደል ዳንኤል ደረቤ ኳስ በሚያገኝበት አጋጣሚ ወደ ሳጥን በመጣል ጫና ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።

በእንቅስቃሴ እጅጉኑ ብልጫ የነበራቸው ፖሊሶች በርካታ ለግብ የተቃረቡ ሙከራዎችን አድርገዋል። 1ኛ ደቂቃ ላይ ብሩክ ኤልያስ ከዘላለም ኢሳይያስ የተቀበላትን ድንቅ ኳስ ላውረንስ ላርቴን አታሎ አልፎ ሲሞክር ተክለማርያም ሻንቆ እንደምንም በእግሩ ሲመልስ ያገኛት በረከት ይስሀቅ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጭ የወጣችበት ፖሊሶች በጊዜ መሪ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ ነበረች። 7ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ይስሀቅ ከሳጥኑ ውስጥ ወደ ኋላ በመመለስ ከሳጥን ውጭ ለነበረው ዘላለም ኢሳይያስ ሰጥቶት በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ ተክለማርያም ሻንቆ በአግዳሚው ለጥቂት አውጥቶበታል። ከዚህች ሙከራ በኋላ ምላሽ የሰጡት ሀይቆች በመልሶ ማጥቃት በተገኘች ኳስ ዳንኤል ደርቤ ለመስፍን ታፈሰ አቀብሎት ወደ ሳጥኑ እየገፋ ቢገባም ግብ ጠባቂው ሀብቴ ከድር ተንሸራቶ በመውረድ ሲያድንበት መስፍን ታፈሰ ከጨዋታ ውጭ ነው በማለት በአንደኛ ረዳት ደኛው ኃይለራጉኤል ወልዳይ ላይ የደቡብ ፖሊስ ቡድን መሪ እና የአሰልጣኝ አባላት ተቃውሟቸውን ገልፀዋል።


ጨዋታውን በአግባቡ በመቆጣጠር በርካታ ሙከራዎች ያደረጉት ፖሊሶች በግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ የግል ብቃት ባይመክኑ ኖሮ በርካታ ግቦች የማግባት አጋጣሚ ነበራቸው። 25ኛው ደቂቃ ዘላለም ኢሳይያስ ከማእዘን ያሻማትን ኳስ ኪዳኔ አሰፋ በጭንቅላቱ ገጭቶ ተክለማርያም በጣቱ ለጥቂት ነክቶ በአግዳሚው ስትመለስ የሀዋሳ ተከላካዮች ተረባርበው ወደ ውጭ አውጥተዋታል። በድጋሚ የተገኘውን የማእዘን ምት አበባው ቡታቆ አሻምቶ ሄኖክ አየለ በጭንቅላቱ ቢገጨውም በድጋሚ የሀዋሳ ተከላካዮች አውጥተውበታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም አበባው ያሻማለትን ኳስ ሄኖክ አየለ በግንባሩ ገጭቶ ተክለማርያም ያዳነበት የምታስቆጭ ሙከራ ነበረች።

ከጥሩ የኳስ ፍሰት ውጭ ጫና መፍጠር ያልቻሉት ሀዋሳዎች የሚያገኟቸውን አጋጣሚ ከመጠቀም ግን ወደኋላ አላሉም። 30ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዮሐንስ ከርቀት አክርሮ በመምታት ድንቅ ግብ አግብቶ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ በኋላ መነቃቃትን ያሳዩት ሀዋሳዎች በድጋሚ 39ኛው ደቂቃ ከሄኖክ ደልቢ በተነሳች ኳስ ደንኤል ደርቤ በቅርቡ ወደ ዋናው ቡድን ላደገው መስፍን ታፈሰ ሰጥቶት በአግባቡ ተቆጣጥሮ ወደ ሳጥን በመግባት በግል ብቃቱ ወደ ግብነት በመቀየር የክለቡን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።

ከጎሎቹ በኋላ ፖሊሶች ሁለት ለግብ የተቃረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በረከት ይስሀቅ ነፃ የማግባት እድል አግኝቶ ያልተጠቀመበት እና አበባው ቡጣቆ ከርቀት አክርሮ መትቶ ቋሚው የመለሰበትም የሚጠቀሱ ናቸው።


በእረፍት ስዓት የተሻ ግዛውን በበረከት ይስሀቅ እና ብርሀኑ በቀለ በኤርምያስ በላይ ቀይረው የማስገባት ውሳኔያቸው ለውጥ ፈጥሮላቸዋል። 47ኛው ደቂቃ የትሻ ግዛው ከአዲሳለም ተስፋዬ እግር ስር በመንጠቅ የተሻ ግዛው በጥሩ አጨራረስ ግብ በማድረግ ልዩነቱን አጥብቧል። በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ የነበረው እና በግሉ ድንቅ እንቅስቃሴን ያሳየው ብሩክ ኤልያስ ከሁለት ደቂቃ በኋላ ከዘላለም ኢሳያስ የተላከችለትን ኳስ በመቆጣጠር የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች ከጨዋታ ውጭ ነው ብለው ሲዘናጉ በድንቅ አጨራረስ ግብ አድርጎ ክለቡን አቻ አድርጓል።


ግብ ካገቡ በኋላ ተጭነው የተጫወቱት ደቡብ ፖሊሶች በየተሻ አማካኝነት ግብ አግብተው ከጨዋታ ውጭ ተብሎባቸዋል። ጨዋታውን በድንቅ ብቃት የመሩት አማኑኤል ኃይለስላሴ 67ኛው ደቂቃ አክሊሉ ተፈራ ኪዳኔ አሰፋ ላይ በሰራው አደገኛ ጥፋት በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ሲያሰናብቱት በጎደሎ ለመጫወት የተገደዱት ሀዋሳዎች ግብመ አስተናግደዋል። 78ኛው ደቂቃ የተሻ ግዛው በድጋሚ ከአዲስዓለም ተስፋዬ እግር ስር በመንጠቅ የክለቡን የማሸነፊያ ግብ ማስቆጠር ችሏል።


በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ምንተስኖት አበራ ኪዳኔ አሰፋን በክርኑ በመማታቱ በቀጥታ በቀይ ካርድ ከሜዳ ለመወገድ ተገዷል። በጨዋታው መገባደጃ ብሩክ ኤልያስ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ሄኖክ አየለ ወደ ሳጥን እየገፋ በመግባት ያልተጠቀመባት የጨዋታው ማሳረጊያ ግብ ልትሆን የምትችልበት አጋጣሚ ነበረች። በዚህ መሰረት ደቡብ ፖሊስ 3-2 በማሸነፍ ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ ወደ አሸናፊነት መመለስ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡