የወንድወሰን ዮሐንስ ስርዓተ ቀብር ዛሬ ተፈፀመ

ከትላንት በስቲያ ምሽት እግር ኳስን በሚጫወትበት ነቀምት ከተማ በተተኮሰ ጥይት ህይወቱ ያለፈው ወንድወሰን ዮሐንስ ስርዓተ ቀብር ዛሬ በሀዋሳ ቅድስት ሥላሴ ቤተ-ክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡

በ1983 በሀዋሳ ከተማ በተለምዶ ኮረም ተብሎ በሚጠራ ስፍራ የተወለደው ዮሐንስ በዛው በሰፈሩ በሚገኘውና በርካታ ተጫዋቾችን ማፍራት በቻለው ኮረም ሜዳ ላይ እግር ኳስን በፕሮጀክት ደረጃ መጫወት ጀምሮ ለሀዋሳ ከተማ የውስጥ ውድድሮችን በየእድሜ እርከኖች ከተጫወተ በኃላ ደቡብ ክልልን በመወከል ከ17 ዓመት በታች በሀገር አቀፍ ደረጃ በተደረገ ውድድር ላይ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በወቅቱ በሚመራው ደቡብ ፓሊስ ውስጥ 2004 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የክለብ ህይወትን የጀመረው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ በመቀጠል በሌሎቹ የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ስልጤ ወራቤ እና የቀድሞው ውሀ ስራ በአሁኑ ኢኮስኮ ክለብ መጫወት ችሏል፡፡ ቡታጅራ ከተማን 2009 ከለቀቀ በኃላም ከተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ጀምሮ ህይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በነቀምት ከተማ ውስጥ በርካታ ጨዋታዎች ላይ ቋሚ ተሰላፊ በመሆን ክለቡ ውጤታማ እንዲሆን አስችሏል፡፡

ከትናንት በስቲያ ግንቦት 28 ረፋድ ከቡድን አባላቱ ጋር ልምምድ ያደረገ ሲሆን ዕሁድ ከአርባምንጭ ጋር ለሚደረገው የከፍተኛ ሊግ ጨዋታም አሰልጣኙ በመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ሊያካትተው እንደነበር የቡድን ጓደኞቹ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል። ሆኖም ምሽት 12:30 ላይ የክለቡ ተጫዋቾች እንደ ወትሯቸው የእራት ሰአት ደርሶ በሚመገቡበት ሆቴል ተመግበው በመውጣት ላይ ሳሉ በአካባቢው በተፈጠረ ሁከት ቦምም መጣሉን የሰሙት የክለቡ ተጫዋቾች ራሳቸውን ለማዳን ሲዋከቡ ሟቹ ወንድሰን በድንጋጤ ለመሸሽ ሲል በፓሊስ በተተኮሰ ጥይት ተመትቶ ወደ ሆስፒታል ቢያመራም ህይወቱን ማትረፍ ሳይቻል ቀርቷል፡፡

የ28 ዓመቱ ወጣቱ ወንድወሰን ዮሐንስ በተወለደበት ሀዋሳ ከተማ ዛሬ ረፋድ 5:00 ላይ በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ቤተሰቦቹ፣ ዘመዶቹ፣ በርካታ የስፖርት ሰዎች፣ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ የተጫወተባቸው ክለብ አመራሮች፣ የክለብ ጓደኞቹ እንዲሁም ወዳጆቹ በተገኙበት የቀብር ስነ-ሥርዓቱ ተፈፅሟል፡፡

ትዳር ያልመሠረተው ወንድወሰን አባቱን ካጣ በኋላ ከሰባት በላይ ወንድም እና እህቶቹን በብቸኝነት ያስተዳድር እንደነበር ሶከር ኢትዮጵያ ከተጫዋቹ ወዳጆች በስፍራው ተገኝታ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡