ኳታር 2022| የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋዜጣዊ መግለጫ…

ለኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ ማጣርያ የሌሶቶን ብሔራዊ ቡድን የሚያስተናግዱት ዋሊያዎቹን ዝግጅት አስመልክቶ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ እና አምበሉ ሽመልስ በቀለ በዩኒሰን ኢንተርናሽናል ሆቴል በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ያነሷቸውን ዋና ዋና ነጥቦች እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ

ስለ ዝግጅታቸው

ከሌሶቶ ጋር ላለው ቅድመ ማጣሪያ መደልደላችንን ካወቅን ጊዜ አንስቶ በባህር ዳር ልምምዳችን ስናደርግ ቆይተናል። ነሀሴ 16 ሀሙስ ወደ ባህር ዳር ጉዞ አድርገን ከገባንበት ቀን ጀምሮ ከሰዓት ልምምድ የጀመርን ሲሆን ለአንድ ሳምንት በቀን ሁለት ጊዜ አየሰራን ቆይተናል። ሁላችሁም እንደምታውቁት ተጫዋቾች በሌላው ዓለም የሊግ ውድድር ጨርሰው ወደ ብሔራዊ ቡድን ሲሄዱ የልምምድ ጫና ስለሚቀንስ የቅንጅት ስራ ላይ ነው የሚያተኩሩት። የኛ ሀገር ሊግ ግን የመቆራረጥ ችግር ስለነበረው በተጫዋቾች ብቃት ላይ የመዘበራረቅ ወይም ተፅዕኖ ይታይ ነበር። እሱን ለመቅረፍ በቀን ሁለት ጊዜ ስንሰራ ቆይተናል ። በባህር ዳር እግርኳስ ፌደሬሽን በጣም ጥሩ ከሆነ አቀባበል ጀምሮ ሜዳውን በአግባቡ ዝግጁ እስከማድረግ ጥሩ ድጋፍ አድርገውልናል። እንዲሁም ያረፍንበት ሆቴል ደረጃውን የጠበቀ መሆኑ ክልሎች ለአህጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ውድድር መስተንግዶ ብቁ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።

ከጂቡቲው የቻን የማጣሪያ ጨዋታ ላይ ክፍተቶች እና የተወሰዱ እርምቶች

ከጂቡቲው ጨዋታ እርምቶች ተወስደዋል። በስነልቦና ደረጃ ከባለሞያዎች ጋር በመነጋገር ድጋፍ አድርገናል። ሁለተኛው በጅቡቲ ጨዋታ በነበረው እንቅስቃሴ ተጫዋቾችም እኔም ደስተኛ አልነበርነም። ያ ነገር የፈጠረው ከፍተኛ ቁጭት ተግተው እንዲሰሩ አድርጓቸዋል። በጅቡቲው ጨዋታ ላይ ከፍተኛ ክፍተት የነበረው በመከላከሉ ላይ ነበር። የታዩ ጉልህ ስህተቶችን እነሱን አርመን እንገባለን።

በውጭ ሀገራት ስለሚገኙ ተጫዋቾች

በተደጋጋሚ እንደተናገርኩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ በሌሎች ሀገራት እንደሚደረገው በውጭ የሚጫወቱት ተጫዋቾች ሀብት አጠቃቀም ላይ መስተካከል አለብን። የግብፁ አፍሪካ ዋንጫ ላይ እንዳየሁት በአማካይ 70 ፐርሰንት የሚሆኑት ከውጭ የሚገኙ ተጫዋቾች ናቸው። ለምሳሌ እንኳን ማዳጋስካር እና ብሩንዲ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፈው አብዛኞቹ ተጫዋቾች በውጭ ሀገራት የሚጫወቱ ናቸው ። የኛ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች አብዛኞቹ ፍቃድ ስላላገኙ ነው ወደ ኢትዮጵያ ያልመጡት። የሀገሪቱ ፌዴሬሽን ላይ ፍቃድ አግኝተው ክለቡ ፈቅዶላቸው ፊፋ ለኢትዮጵያ እንዲጫወቱ ፍቃድ ባለመስጠቱ ተጫዋቾቹ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አልቻሉም። ኢትዮጵያ ይህን እድል በመስጠቷ ብዙ በውጭ የሚጫወቱ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ ደውለውልኛል፤ በጣም ደስተኛ ሆነዋል። ለቼክ ሪፐብሊክ የተጫዎተው ቴዎዶር ገ/እግዛብሄር ደውሎልኝ ለኢትዮጵያ መጫወት ይፈልግ እንደነበርና ለቼክ በመጫወቱ ምክንያት ይሄን እድል እንዳጣው በቁጭት ስሜት ነበር የነገረኝ። ሌሎች ተጫዋቾችም ይሄን እድል ማግኝታቸው በራሱ ጥሩ እንደሆን አውርተን ነበር።

መልዕክት

የባህር ዳር እና አካባቢው ህዝብ በሜዳ ተገኝቶ እንዲደግፈን ጥሪዬን አቀርበዋለሁ። እውነት ለመናገርም የባህር ዳር ህዝብ ጥሪ የሚያስፈልገው አይደለም። በመቀጠል በሜዳ ተገኝተው አቀባበል ላደረጉልን የባህር ዳር ደጋፊዎች ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በተለይ ደግሞ ስታዲየሙን ጠዋት እና ማታ ሲንከባከቡት ለቆዩት ሰዎች፤ ድጋፍ ሲሰጡን ለቆዩት የስፖርት ቤተሰቦች እና የመንግስት አካላት ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

ሽመልስ በቀለ

ስለ ዝግጅት እና የቡድኑ መንፈስ

ቀደም ሲል አሰልጣኙ እንደተናገረው ለዚህ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በኋላም ላለው ጨዋታዎች ነው እየተዘጋጀን ያለነው። እኔ ከመጣሁ አንስቶ፤ በተጨማሪም ተጫዋቾቹ በቻን ውድድር ላይ የቆዩ ስለነበሩ ከውጭ የመጣነው ተጨምረን እየሰራን ነው። ከሞለ ጎደል ጥሩ ነገር አለ። ለዚች ሀገር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ጥሩ ነገር የሚያሳዩ ተጫዋቾች አሉን።

መልዕክት…

በነገው ጨዋታ እናንተ ከዚህ ስለተገኛችሁ ብቻ ትገባላችሁ ማለት አይደለም፤ አትገቡም ማለትም አይደለም። ባላችሁ ሙያ የበኩላችሁን ድጋፍ መድረግ ትችላላችሁ። ለምሳሌ እኔ ስለ ቻን ማጣሪያ ሰምቻለሁ፤ ኢትዮጵያ አሸነፈች
ከሚለው በላይ ኢትዮጵያ 3 ገባባት ነው ሲባል የነበረው። ይህም ለተጫዋቾች ስነ-ልቦና ጥሩ አይደለም። ለሀገርም ጥሩ አይደለም። እኛ የምንችለውን እንሰራለን፤ እናንተም በሙያችሁ ለሀገሪቱ እግርኳስ እድገት ድጋፍ አድርጉ ።


© ሶከር ኢትዮጵያ