ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከድል መልስ ዝግጅቱን እየከወነ ይገኛል

በፓናማ እና ኮስታሪካ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ወደ ቡጁንቡራ በማቅናት ቡሩንዲን በሰፊ የግብ ልዩነት ያሸነፍው ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑ ለመልሱ ጨዋታ ዝግጅቱን እየሰራ ይገኛል።

ባለፈው ሳምንት ከሜዳው ውጭ ቡሩንዲን 5-0 በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ዕድሉን አስፍቶ የተመለሰው በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል እና ህይወት አረፋይኔ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣይ ሳምንት በባህር ዳር ስታዲየም ላለበት የመልስ ጨዋታ በኢትዮጵያ ሆቴል ማረፊያውን በማድረግ በአዲስ አበባ ስታዲየም ልምምዱን እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራ ቡድኑን ለመቀላቀል ወደ ባህር ዳር ያቀኑት አረጋሽ ካልሳ፣ ገነት ኃይሉ፣ ይመችሽ ዘውዴ እና ነፃነት ፀጋዬ ከቡድኑ ጋር አብረው የማይገኙ ተጫዋቾች ናቸው። በመጀመርያው ጨዋታ ከ18ቱ ተጫዋቾች ስብስብ ውጭ በመሆን ወደ ቡሩንዲ ያልተጓዘችው የሀዋሳዋ አጥቂ ነፃነት መና አሁን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ተቀላቅላ ልምምድ እየሰራች ትገኛለች።

15 ተጫዋቾችን በመያዝ ልምምዱን እየሰራ የሚገኘው ብሔራዊ ቡድኑ የፊታችን እሁድ ማለዳ የመልሱን ጨዋታ ወደሚያደርግበት ባህር ዳር ከተማ በማቅናት ልምምዱን ሲሰራ ቆይቶ ጥር 24 ቀን የመልሱን ጨዋታ የሚያደርግ ይሆናል። በደርሶ መልስ ውጤት ብሔራዊ ቡድኑ ስኬታማ ከሆነ በቀጣዩ ዙር የሞዛምቢክ እና የዚምባባዌ አሸናፊን የሚገጥም ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ