የሴቶች ገፅ | “ከሁለት ልጆቼ ጋር እየተጫወትኩ ነው ቀኑን የማሳልፈው” ሰርካዲስ እውነቱ

አሰልጣኝ ሰርካዲስ እውነቱን ይህንን የኮሮና ወቅት እንዴት እያሳለፈች እንደሆነ በሴቶች ገፅ አምዳችን አጫውታናለች።

ውልደት እና እድገቷ ባህር ዳር ከተማ ልዩ ሥሙ አየር ሜዳ በሚባል ቦታ ላይ ነው። ከልጅነቷ ጀምሮ በሰፈር ውስጥ በሚገኝ ሜዳ እግርኳስን ትጫወት የነበረችው ሰርካዲስ ለረጅም ዓመታት ለባህር ዳር ልዩ ዞን እና ለአማራ ክልል ምርጥ በመጫወት አሳልፋለች። “ሴትን ልጅ ከወንድ የተሻለ ሴት ብታሰለጥናት የተሻለ ነው” በሚል ሃሳብ ተገፋፍታ ወደ ሴቶች አሰልጣኝነት የገባችው ሰርካዲስ በተለይ ተጨዋች እያለች ሴቶችን ወንዶች ሲያሰለጥኑ ያለውን ክፍተት ታዝባ ወደ ሙያው እንደገባች ትናገራለች። የባህር ዳር ዞን፣ የአማራ ክልል፣ ዳሽን ቢራ፣ ጥረት ኮርፖሬትን አሁን ከምትገኝበት ባህር ዳር ከተማ የሴቶች ቡድን በፊት አሰልጥናለች። ሰርካዲስ ከአምስቱ ክለቦች በተጨማሪ በሁለት የተለያዩ አጋጣሚዎች ከ20 እና ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ በመሆን አገልግላለች (አሁንም ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድኑ ረዳት ነች)። ወደ አሰልጣኝነት ህይወት ባልገባ ኖሮ “የተዋጣልኝ ነጋዴ” እሆን ነበር የምትለው ሰርካዲስ ይህንን የኮሮና ወቅት እንዴት እያሳለፈች እንደሆነ በአጭሩ አጫውታናለች።

“ብዙ ጊዜ የእግርኳስ አሰልጣኝነት እንደ ወንድ ስራ ነው የሚቆጠረው። ይህ ግን ልክ አደለም። እኔ ከኮሮና በፊት ረጅም ሰዓቶቼን ሜዳ ላይ ነበር የማሳልፈው። ከሜዳም ከተመለስኩ በኋላ የተለያዩ ጉዳዮች ስለማይታጡ እነሱን ለማስጨረስ ስሯሯጥ እውላለሁ። በዚህ ምክንያት ከኮሮና በፊት ቤት ላይ ብዙ ጊዜ አልነበረኝም ነበር። ከቤተሰቦቼ ጋርም ብዙ ጊዜዎችን አናሳልፍም ነበር። አሁን ግን በዚህ አስከፊ በሽታ ምክንያት ውሎዬ ቤት ሆኗል። ከሁለት ልጆቼ ጋር እየተጫወትኩ ነው ቀኑን የማሳልፈው። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ሴት ልጄን ከወለድኩ ገና 6 ወሬ ስለሆነ እሷን እየተንከባከብኩ ጊዜዬን አሳልፏለሁ። ይህን ስልህ ግን የክለብ ልጆቼን ረስቻለው ማለቴ አደለም። ከተጨዋቾቼ ጋርም በስልክ ብዙ ነገሮችን እናወራለን። በአጠቃላይ ወረርሽኙ አስከፊ ቢሆንም እኔ ግን እየተጠነቀኩ በቤቴ ጥሩ ጊዜን እያሳለፍኩ ነው።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: