ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| አርባምንጭ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| አርባምንጭ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

34ኛው ሳምንት በደረጃ ሰንጠረዡ ተከታትለው የተቀመጡትና በሁለት ነጥቦች የሚበላለጡ አዞዎቹ እና ፈረሰኞቹ ደረጃቸውን ለማሻሻል በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል።

በአርባ ሁለት ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዞዎቹ የተያያዙት የድል መንገድ በማስቀጠል ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ጫና ውስጥ ከከተቱት ስምንት አስከፊ የጨዋታ ሳምንታት መልስ ሁለት ወሳኝ ድሎች አስመዝግቦ ላለመውረድ ከሚደረገው ፍልምያ ቀስ በቀስ ራሱን እያራቀ የመጣው አርባ ምንጭ ከተማ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቦ በጊዜያዊነትም ቢሆን ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ለማለት የነገውን ጨዋታ ይፈልገዋል። አዞዎቹ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በተነሳሽነት እንዲሁም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የሚታይ ለውጥ አምጥተዋል፤ የተመዘገቡ ውድ ስድስት ነጥቦች በሊጉ አናት ላይ ተከታትለው የተቀመጡትን ቡድኖች ባገኙባቸው መርሐ-ግብሮች መሆናቸው ደግሞ ቡድኑ ጥሩ መሻሻል እንዳሳየ አመላካች ናቸው።

ኢትዮጵያ ቡና ላይ ድል ባደረጉበት ጨዋታ ጥንቃቄ በተሞላበት አኳኋን የቀረቡት አዞዎቹ ምንም እንኳን በዕለቱ የነበራቸው የማጥቃት እንቅስቃሴ አመርቂ የሚባል ባይሆንም የመከላከል አደረጃጀታቸው ጥንካሬ ሙሉ ነጥብ ይዘው እንዲወጡ አስችሏቸዋል። ቡድኑ ከድል ጋር በተራራቀባቸው ሰባት መርሐ-ግብሮች ላይ ካስቆጠራቸው ድምር ግቦች የሚልቅ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በማስቆጠር መጠነኛ መሻሻል ማሳየት ቢችልም የማጥቃት አጨዋወቱ ጥራት አሁንም መሻሻል የሚገባው ነው።

ከሦስት ተከታታት ሽንፈቶች በማገገም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ በማሳካት በአርባ አራት ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ ለማለት ድልን እየለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ፈረሰኞቹ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገው ከመሪው መድን ጋር ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ላይ የነበራቸው የመከላከል ብርታት የሚያስወድሳቸው ነበር። ቡድኑ በተለይም ተከታታይ ሽንፈቶች ባስተናገደባቸው ጨዋታዎች ላይ የነበሩበትን የመከላከል ክፍተቶች በማረም በዕለቱ የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ቡድን መቋቋም መቻሉ በመልካም ጎኑ ይጠቀስለታል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጀመርያዎቹ እና በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ የተሰነዘሩባቸውን ጥቃቶች በመመከት ረገድ ካሳዩት ብቃት በተጨማሪ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ ደቂቃዎች ላይ ጥቂት የማይባሉ የግብ ዕድሎች መፍጠር ችለው ነበር። ውስን ብልጫ በወሰዱባቸው ደቂቃዎች ያገኟቸውን የግብ ዕድሎች በመጠቀም ረገድ የነበራቸው ብቃትም በነገው መሻሻል የሚገባው ነው።

በመጨረሻው ጨዋታ ጠንካራውን የመድን የማጥቃት አጨዋወት በተሻለ መንገድ ለመመከት ወደ መከላከሉ ያዘነበለ አቀራረብ የነበራቸው ፈረሰኞቹ የነገው ተጋጣሚያቸው ቀጥተኛ አቀራረብ ያለው እና ከኳስ ጋር ዘለግ ያለ ጊዜ የማሳለፍ አዝማሚያ የማይታይበት ቡድን ስለሆነ ከባለፈው በተሻለ መንገድ ኳሱን ለመቆጣጠር ጥረት ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል።


በአርባምንጭ ከተማ በኩል ግብ ጠባቂው ኢድሪሱ ኦጎዶጆ፣ እንዳልካቸው መስፍን እና በላይ ገዛኸኝ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆናቸውን አረጋግጠናል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አማኑኤል ተርፉ እና ተገኑ ተሾመ አሁንም በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው ። ፈረሰኞቺ አማካዩ አብርሀም ጌታቸው እና አጥቂውን ፍፁም ጥላሁንን በቅጣት ቢያጡም ያለፉት ሁለት ጨዋታዎች በቅጣት ምክንያት ያልነበረውን ሌላኛውን አጥቂ አማኑኤል ኤርቦን ማግኘታቸው መልካም ዜና ሲሆን ሌሎቹ የቡድኑ አባለትም ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው አውቀናል።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ በ19 አጋጣሚዎች እርስ በእርስ የተፋለሙ ሲሆን በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስ 13 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው አርባምንጭ ከተማ በአንፃሩ 2 ጊዜ ድል አድርጎ የተቀሩት 4 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተፈፅመዋል።