በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን የሚካሄዱ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተናል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ሽረ ምድረ ገነት
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ለመጠጋት የሚጥሩት ኤሌክትሪኮች እና በሊጉ በጥሩ መሻሻል ላይ የሚገኙት ምድረ ገነት ሽረዎች የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።
ባለፉት 5 ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ሽንፈት የገጠማቸው በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በ17 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ቡድኑ ምንም እንኳን በሊጉ አንድ ጊዜ ብቻ ሽንፈትን ቢያስተናግድም ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ ግን አሸናፊነታቸውን ለማስቀጠል እንቅፋት ሆኖባቸዋል። ባለፈው ሳምንት ከመቻል ጋር ያደረጉት ጨዋታ 0ለ0 መጠናቀቁን ተከትሎ ዛሬ ወደ ድል ለመመለስና ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በአንጻሩ ምድረ ገነት ሽረዎች ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ እያሳዩት ያለው መረጋጋት የሚደነቅ ነው። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ምንም ዓይነት ሽንፈት ያላስተናገዱት ሽረዎች በጨዋታዎቹ ሊገኙ ከሚችሉ 15 ነጥቦች 9ኙን በመሰብሰብ በ14 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ልክ እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ባለፈው ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ ያለምንም ግብ 0ለ0 መጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን የዛሬው ጨዋታ ጥሩ የሆነ ጉዟቸውን ለማስቀጠል ትልቅ ፈተና ይሆንባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ለረጅም ጊዜ ከሜዳ የራቀው ተከላካዩ አብዱላሂ አላዩ እና አጥቂው አብነት ተስፋዬ በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው። ሽረ ምድረገነቶች በአንጻሩ ጸጋአብ ዮሐንስን ብቻ በጉዳት ያጣሉ።
ሁለቱ ቡድኖች ቀደም ሲል በሊጉ ሁለት ጊዜ ብቻ የተገናኙ ሲሆን፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አንድ ጊዜ ድል ሲቀዳጅ በቀረው አንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ኤሌክትሪኮች አንድ ግብ ሲያስቆጥሩ፣ ሽረዎች ግን በግንኙነታቸው ግብ ማስቆጠር አልቻሉም።
ሸገር ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ
ወደ ድል ለመመለስ የሚጥሩት ሸገር ከተማ እና የደረጃ ሰንጠረዡ መሪዎች ላይ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማ በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ በ11ኛ ሳምንት መርሐግብር ይገናኛሉ።
በሊጉ አዲስ አዳጊ የሆነው ሸገር ከተማ ይሄ ነው ሊባል የሚችል ወጥ የሆነ አቋም እያስመለከተን ያልሆነ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በ12 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑ በተለይም ባሳለፍነው ሳምንት በወላይታ ድቻ የደረሰበት የ3ለ1 ያልተጠበቀ ሽንፈት የቡድኑን የመከላከል አደረጃጀት ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነበር። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች 7 ነጥብ መሰብሰብ የቻለው ሸገር ከተማ ዛሬ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ብርቱ ፉክክር ማድረጉ አይቀሬ ነው።
በአንጻሩ ሀዋሳ ከተማዎች በ17 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የደረጃ ሰንጠረዡን አናት እየተከተሉ ይገኛሉ። ምንም እንኳን ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ላይ ወጥ የሆነ አቋም ለማሳየት ሲቸገሩ ቢታዩም፣ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ መድንን 2ለ1 በማሸነፍ ያገኟቸው ሦስት ነጥቦች ለዛሬው ጨዋታ ትልቅ መነቃቃትን ይፈጥርላቸዋል። የዛሬው ጨዋታ ለሐይቆቹ በደረጃ ሰንጠረዡ ይበልጥ ወደ ላይ ለመጠጋት ወሳኝ በመሆኑ፣ በማጥቃት ረገድ ያላቸውን ብቃት ተጠቅመው የሸገርን መከላከል አቅም ለመፈተን እንደሚሞክሩ ይጠበቃል።
በሸገር ከተማም ሆነ በሀዋሳ ከተማ በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው በሊጉ መድረክ ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያቸው ይሆናል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ
መነቃቃት ላይ የሚገኙት “ቡናማዎቹ” እና ከድል ጋር ከተራራቁ የሰነበቱት “ብርቱካናማዎቹ” የሚያደርጉት ፍልሚያ በሊጉ 11ኛ ሳምንት መርሐግብር ከሚጠበቁ ጨዋታዎች አንዱ ነው።
ባለፈው የውድድር ዓመት በሊጉ ካሳየው ድንቅ ብቃት አንጻር ዘንድሮ የሚጠበቅበትን ያህል መጓዝ የከበደው ኢትዮጵያ ቡና፣ በ12 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሆኖም ቡድኑ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች 8 ነጥቦችን መሰብሰብ መቻሉ በመጠኑም ቢሆን መነቃቃት ላይ መሆኑን ያሳያል። ባለፈው ሳምንት ከወልዋሎ ዓ/ዩ ጋር 1ለ1 ተለያይተው ነጥብ የተጋሩት ቡናማዎቹ፣ ዛሬ ወደ አሸናፊነት በመመለስ ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ። በተለይም የተጫዋቾቹ የመናበብ ሂደት እየተሻሻለ መምጣቱ ለአሰልጣኙ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው።
በአንጻሩ ድሬዳዋ ከተማዎች በ13 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው 3 ነጥብ ማግኘትን በናፍቆት ይጠብቃሉ። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ምንም ዓይነት ድል ማጣጣም ያልቻሉት ብርቱካናማዎቹ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ደግሞ አቻ በመለያየት የአንድ ነጥብ ጉዟቸውን ቀጥለዋል። ልክ እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ባለፈው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር 1ለ1 የተለያዩት ድሬዳዋዎች፣ የድል ድርቃቸውን ለመስበርና ከአቻ ውጤት ለመላቀቅ ዛሬ ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል ግብ ጠባቂው ዳንላድ ኢብራሂም እና ረጀብ ሚፍታህ በጉዳት የማይኖሩ ሲሆን ወልደአማኑኤል ጌቱ ፣ ይታገሱ ታሪኩ እና አማኑኤል አድማሱ ግን ከጉዳት ተመልሰው ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ሆነዋል። ድሬዳዋ ከተማ አብዱልሰላም የሱፍን በቅጣት እንዲሁም አቤል አሰበ እና አስቻለው ታመነን በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ሲያደርግ አማካዩ አቡበከር ሻሚል ግን ከቅጣት መልስ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ተጠቁሟል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 26 ጊዜያት ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 15 በማሸነፍ ሰፊ የበላይነት ይዟል። 6 ጨዋታ አቻ የተጠናቀቀ ሲሆን ድሬዳዋ 5 ጨዋታ አሸንፏል። ቡናማዎቹ 44፣ ብርቱካናማዎቹ 24 ጎሎች አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን አልተካተተም)
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በሊጉ 11ኛ ሳምንት መርሐግብር ከፍተኛ ትኩረት የሚስበው ጨዋታ በመዲናዋ አዲስ አበባ ተወካዮች በሆኑት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መካከል በአሳቴዩ ስታዲየም ይካሄዳል።
የውድድር ዓመቱን መልካም በሚባል ጅማሮ አድርገው የነበሩት ፈረሰኞቹ ባለፉት ሳምንታት ግን ባልተለመደ ሁኔታ የአቋም መውረድ እየታየባቸው ይገኛል። በ16 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ፈረሰኞቹ፣ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው 15 ነጥቦች 4 ነጥቦችን ብቻ መሰብሰባቸው ቡድኑ ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ማሳያ ነው። ባለፈው ሳምንት ከሲዳማ ቡና ጋር በነበራቸው ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ በሀብታሙ ጉልላት አስደናቂ ግብ 1ለ1 ተለያይተው ነጥብ ቢጋሩም፣ ቡድኑ ወደ ቀደመው አስፈሪነቱ ለመመለስ ዛሬ የግድ ማሸነፍን ምርጫው ማድረግ ይኖርበታል።
በአንጻሩ የ2016 የሊጉ ሻምፒዮን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከከባድ የውጤት መጥፋት በኋላ ወደ ድል መመለስ ችሏል። ለተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ተስኗቸው የነበሩት ባንኮቹ ባለፈው ሳምንት አርባምንጭ ከተማን 3ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከናፈቃቸው ድል ጋር ታርቀዋል። በአሁኑ ወቅት በ11 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ቢቀመጡም፣ ያገኙት ድል በቡድኑ ውስጥ ያለውን በራስ መተማመን ከፍ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል። አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ዛሬም ያንን የድል ጉዞ በመቀጠል ከደረጃው ግርጌ ለመውጣት ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል መሳፍንት ጳውሎስ በጉዳት የማይኖር ሲሆን አቤል ያለው እና አሚኑ ነስሮ ወደ ልምምድ የተመለሱ ቢሆንም ለዛሬው ጨዋታ ብቁ የመሆናቸው ነገር አጠራጣሪ ነው። በንግድ ባንክ በኩል ካሌብ አማንክዋህ ከቅጣት፣ አስጨናቂ ጸጋዬ ከጉዳት ሲመለሱ እንዳለ ከበደ፣ ቢኒያም ካሳሁን እና በዛብህ ካቲሶ በጉዳት አይኖሩም።
ተጋጣሚዎቹ በሊጉ በነበራቸው 39 ያህል ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፍተኛ የበላይነት ያለው ሲሆን 25 አሸንፎ ፣ በ10 ጨዋታ አቻ ተለያይተው ንግድ ባንክ 4 ጨዋታ አሸንፏል። ፈረሰኞቹ 71 ጎሎች ሲያስቆጥሩ ሀምራዊዎቹ 23 ጎሎች አስቆጥረዋል።

