ሀድያ ሆሳዕናዎች በጫላ ተሺታ ብቸኛ ግብ ሀይቆቹን ሲረቱ ሲዳማ ቡናዎችም ሸገር ከተማን በማሸነፍ የሊጉ መሪነት መልሰው ተረክበዋል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም በተካሄደ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ነብሮቹ መጠነኛ ብልጫ የወሰዱበት ነበር።
ከመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ጀምሮ ጫና በመፍጠር
የግብ ዕድሎችን የፈጠሩት ነብሮቹም በ22ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። ኤልያስ አሕመድ በረዥሙ ተሻግራ የሀዋሳ ከተማ ተከላካይ የጨረፋት ኳስን በጥሩ መንገድ ለኢዮብ አለማየሁ ካቀበለው በኋላ አጥቂው ብቻውን ተነጥሎ ለነበረው ጫላ ተሺታ አመቻችቶለት ተጫዋቹ ተረጋግቶ ከመረብ ጋር ያዋሀዳት ኳስም ነብሮቹን መሪ ማድረግ ችላለች።
በአጋማሹ በመሀል ሜዳ ብልጫ የተወሰደባቸው ሀዋሳ ከተማዎችም ሙከራዎች ለማድረግ ተቸግረው ከቆዩ በኋላ አስቆጪ ዕድል መፍጠር ችለዋል። ከያሬድ ብሩክ እና ብሩክ ታደለ ጥሩ ቅብብል በኋላ ሳጥን ውስጥ የነበረው ጌታነህ ከበደ እግር ደርሳ አጥቂው ወደ ግብ ከመምታቱ በፊት ተፈራ አንለይ ያጨናገፋት ኳስም በአጋማሹ ሀይቆቹ የፈጠሯት የተሻለች የግብ ዕድል ነበረች።

ሁለተኛው አጋማሽ ቡድኖቹ ተጠናክረው ቀርበው የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ያደረጉበት ነበር። በሀዋሳ ከተማዎች በኩል አብነት ደምሴ በመልሶ ማጥቃት የተገኘችውን ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቷት በግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለ የተመለሰች ኳስ ፤ በሀድያ ሆሳዕናዎች በኩል ደግሞ ኢዮብ አለማየሁ በመስመር በኩል ይዟት የገባውን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ ተጠቃሾች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ሄኖክ አርፊጮ ከቆመ ኳስ በቀጥታ መቷት ሰይድ ሀብታሙ ጨርፎ ያወጣት ሙከራም የነብሮቹ መሪነት ለማጠናከር የተቃረበች ነበረች። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን በመጀመሪያ አጋማሽ ላይ በተቆጠረች ብቸኛ ግብ ለነብሮቹ ሙሉ ሶስት ነጥብ በማስገኘት ተቋጭቷል።

ሲዳማ ቡና ከ ሸገር ከተማ
ተጠባቂ የነበረው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በፈጣን እንቅስቃሴዎች የታጀበ ነበር። ሲዳማ ቡናዎች በአጋማሹ ፈጣን አጀማመር በማድረግ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል በሚታይባቸው ከፍተኛ መቻኮል ኳስና መረብ ማገናኘት አልቻሉም። ከነዚህ ውስጥ ብርሃኑ በቀለ በሁለት አጋጣሚዎች ያደረጋቸው ሙከራዎች ተጠቃሽ ሲሆኑ በተለይም ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቷት ባህሩ ነጋሽ እንደምንም ጨርፎ ወደ ውጭ ያወጣት ሙከራ ለግብ የቀረበች ናት። በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመ እንቅስቃሴ የነበራቸው ሸገር ከተማዎችም በአጋማሹ ይህ ነው የሚባል የጠራ ዕድል መፍጠር አልቻሉም።
ሁለተኛው አጋማሽም በተመሳሳይ የሲዳማ ቡናዎች
ብልጫ የታየበት ሲሆን በ52ኛው ደቂቃም ከተደጋጋሚ ጥረቶች በኋላ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። መስፍን ታፈሰ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን አሻግሯት ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም ሲዳማ ቡናን መሪ ማድረግ ችላለች። ሂደቱም የብሌስ ናጎ እንቅስቃሴ የታከለበት ነበር። ከግቡ መቆጠር በኋላ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ በረጃጅም ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ሸገር ከተማዎች 74ኛው ደቂቃ ላይ ሙአዝ ጋሊ ከመስመር አሻምቷት ያሬድ መኮንን ፍጥነቱን ተጠቅሞ መቷት ኢማኑኤል ካል ባዳናት ኳስ ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር።

ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በተመስገን በጅሮንድ ከሳጥን ውጪ ጠንካራ ሙከራ ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎች
79ኛው ደቂቃ ላይ እፎይታ የፈጠረላቸውን ሁለተኛ ግብ አስቆጥረዋል።ፍቅረየሱስ ተወልደ ብርሃን ከሳጥኑ ጠርዝ ሆኖ መሬት ለመሬት አሻግሯት መስፍን ታፈሰ ተከላካዮች አታሎ በማለፍ በግሩም አጨራረስ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም የሲዳማ ቡናን መሪነት አጠናክራለች። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በሲዳማ ቡና 2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ከሶስት ተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ ድል ያደረገው ሲዳማ ቡና የሊጉ መሪነትም ከፋሲል ከነማ ተረክቧል።

