የጦና ንቦቹ ሁለት የውጭ ዜጎች ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።

በ16 ነጥብ 19ኛ ደረጃ ተቀምጠው የመጀመሪያው ዙር ያጠናቀቁት ወላይታ ድቻዎች ሁለት የውጭ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።
ወደ ቡድኑ ለመቀላቀል የተስማማው የመጀመሪያው ተጫዋች ደግሞ ቤኒናዊው ኢብራሂም ሳሊፉ ነው፤ በኮሶቮ ሱፐር ሊጋ ተሳታፊ ለሆነው ድሪታ በመጫወት ላይ የቆየው እና ከዚህ ቀደም በጋና ክለቦች ‘Techiman Eleven Wonders’ እና ኸርትስ ኦፍ ኦክ ቆይታ የነበረው አማካዩ አሁን ደግሞ በደቡብ ምስራቅ አውሮፓ የነበረውን ቆይታ አጠናቆ ወደ ጦና ንቦቹ ቤት ለማምራት ተስማምቷል። በቅርቡ ዜግነቱ ከጋና ወደ ቤኔን የቀየረው ተጫዋቹ በ2020-21 የጋና ፕሪምየር ሊግ ምርጥ ተጫዋች እና ምርጥ በሀገር ውስጥ የሚጫወት ተጫዋች ሽልማትን ወስዷል። ሁለተኛው ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው ተጫዋች ደግሞ ናይጄርያዊው ኦግስቲን ኦኬጅፓ ነው፤ በኢራቁ አል ኤቲሳላት በመጫወት ላይ የቆየው ይህ የተከላካይ አማካይ ከዚ ቀደም ሲምባን ጨምሮ በሀገሩ ክለቦች ዋሪ ወልቭስ እና ሪቨርስ ዩናይትድ መጫወት ችሏል።
ሁለቱም ተጫዋቾች ወደ ወላይታ ድቻ ለማምራት ከተስማሙ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስብስቡን የተቀላቀሉ ሲሆን ዛሬ ረፋድ ልምምድ እንደሚጀምሩና በቀጣይ ቀናት ደግሞ በይፋ ፊርማቸውን እንደሚያኖሩ ታውቋል።

