ሪፖርት| አዞዎቹ ወሳኝ ድል ሲያሳኩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ባሕርዳር ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት| አዞዎቹ ወሳኝ ድል ሲያሳኩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ባሕርዳር ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

በአበበ ቢቂላ ስታድየም በተካሄዱ የ25ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች አርባምንጭ ከተማ ሸገር ከተማን 2ለ1 ሲያሸንፍ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ባሕርዳር ከተማ ያለ ግብ ተለያይተዋል

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ባሕር ዳር ከተማ

07፡00 ሲል በዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ቀዝቃዛ ፉክክር የተመለከትን ሲሆን በጣና ሞገዶቹ በኩል 6ኛው ደቂቃ ላይ ወንድወሰን በለጠ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት ገብቶ የቀነሰውን ኳስ አማኑኤል ገብረሚካኤል ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።

26ኛው ደቂቃ ላይም የጨዋታው የተሻለው ንጹህ የግብ ዕድል ሲፈጠር አማኑኤል ገብረሚካኤል የሰነጠቀለትን ኳስ ያገኘው አንተነህ ተፈራ በደካማ ሙከራ ኳሱን ለግብ ጠባቂው የሱፍ ሞሩ በቀላሉ አሳቅፎታል።

ከዕረፍት መልስ ኤሌክትሪኮች በመጠኑ ተሻሽለው ሲቀርቡ 60ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ ጥሩነህ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አቤል ሀብታሙ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ሲወጣ 80ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ የመስመር ተከላካዩ መሬት ለመሬት የቀነሰውን ኳስ ፓትሪክ ሲቦማና ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታውም በተለይ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል እጅግ ደካማ እንቅስቃሴ አስመልክቶን ያለ ግብ ተጠናቋል።

ሸገር ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ

10፡00 ላይ በዋና ዳኛ ዓባይነት ሙላት መሪነት በተካሄደው ጨዋታ አዞዎቹ ገና በ3ኛው ደቂቃ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው አሸናፊ ተገኝ በግሩም ሁኔታ በውጪ እግሩ በመምታት ያመቻቸለትን ኳስ ያገኘው አብዱልራህማን መሐመድ ከግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ ጋር ቢገናኝም ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።

19ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልራህማን መሐመድ በግሩም ክህሎት አመቻችቶ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ ካገደበት በኋላ 24ኛው ደቂቃ አርባምንጭ ጨዋታውን መምራት ጀምሯል። ኤፍሬም ታምራት ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ማማዱ ሴክ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር በአዞዎቹ ማልያ መጀመሪያ ጨዋታው የመጀመሪያ ግቡን አስመዝግቧል።

ሸገር ከተማዎች 30ኛው ደቂቃ ላይ ባልታሰበ አጋጣሚ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ዮሴፍ ታረቀኝ ለማሻማት በሚመስል መልኩ ከቀኝ መስመር ያሻገረው ኳስ መረብ ላይ ሊያርፍ ተቃርቦ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ተመልሶበታል።

በጥሩ ፉክክር በቀጠለው ጨዋታ አዞዎቹ 34ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ኤፍሬም ታምራት ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ የሸገሩ ተከላካይ ገዛኸኝ ደሳለኝ ለማስወጣት ሲሞክር ኳሱን የራሱ መረብ ላይ አሳርፎታል።

ከዕረፍት መልስ ተሻሽለው የቀረቡት ሸገሮች ተቀይሮ በገባው ኦዳ መሐመድ አማካኝነት ሁለት ሙከራዎችን ካደረጉ በኋላ 56ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ሄኖክ አዱኛ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ቢኒያም ፍቅሩ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት መረብ ላይ አሳርፎታል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ በአርባምንጭ በኩል አብዱልራህማን ከሳጥን ውጪ ካደረጋቸው ሁለት ሙከራዎች እና በሸገር በኩል ናትናኤል ዘለቀ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሳይጠቀምበት ከቀረው ዕድል ውጪ የተለየ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይፈጠር ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።