ሪፖርት| ማራኪው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ

ሪፖርት| ማራኪው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ

የመጨረሻ ደቂቃ አስገራሚ ትዕይንቶችን ያስመለከተን የሀዋሳ ከተማ እና ወልዋሎ ዓ/ዩ ጨዋታ 2ለ2 ተጠናቋል

በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ መሪነት በሀዋሳ በተካሄደው የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በመጠኑ የተቀዛቀዘ ነበር። 22ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ገብሩ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ያደረገው እና በቀኙ ሳጥን ተጠግቶ በወጣው ጨዋታ የመጀመሪያውን የተሻለ ሙከራ ተመልክተናል።

28ኛው ደቂቃ ላይ ሐይቀቹ መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል። የአብሥራ ደግፌ ከራሱ የግብ ክልል በጥሩ ዕይታ ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ያሬድ ብሩክ ኳሱን ተቆጣጥሮ በግሩም ሁኔታ መረቡ ላይ አሳርፎታል። በቀሪ ደቂቃዎችም በኳስ ቁጥጥሩ ከታየው ፉክክር ውጪ የግብ ዕድሎች ሳይፈጠሩ አጋማሹ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ወልዋሎዎች በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል ተሻሽለው 75ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ገብሩ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ያደረገው ሙከራ በተከላካይ ከተጨረፈ በኋላ ሰዒድ ሀብታሙ አስወጥቶበታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሀዋሳዎች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው የአብሥራ ደግፌ ከቀኝ መስመር በጥሩ ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ጌታነህ ከበደ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።

ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ቢጫዎቹ 82ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ገብሩ ከሳጥን አጠገብ ሞክሮት ሰዒድ ሀብታሙ ከመለሰበት ኳስ በኋላ 86ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ከረጅም ርቀት የተሻገረውን ኳስ ኮንኮኒ ሀፊዝ በግንባሩ ከገጨው በኋላ ኳሱን ያገኘው ነጻነት ገብረመድኅን በድንቅ ሁኔታ ኳሱን አብርዶ በመምታት መረብ ላይ አሳርፎታል።

አስገራሚ ትዕይንቶችን እያስመለከተን በቀጠለው ጨዋታ ወልዋሎዎች 90+2ኛው ደቂቃ ላይ መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል። አፈወርቅ ኃይሉ በረጅሙ ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ዳዊት ገብሩ የግብ ጠባቂውን ሰዒድ ሀብታሙ መውጣት ተመልክቶ ኳሱን በአግባቡ ተጠቅሞ አስቆጥሮታል።

ጨዋታው በወልዋሎ አሸናፊነት የሚጠናቀቅ ቢመስልም ሽመልስ በቀለ ከቅጣት ምት መትቶት ግብ ጠባቂው የናትናኤል ኪዳነ መዘናጋት ተጨምሮበት ኳሱ የወልዋሎ መረብ ላይ በማረፉ ጨዋታው 2ለ2 ሊጠናቀቅ ችሏል።