“ይሄ የእኔ ዕድል ብቻ አይደለም ፤ የማሳድጋቸው 40 ልጆች ዕድልም ነው።” ሸዋረጋ ደስታ
የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት የ44ኛ ዙር አድማስ ዲጂታል ሎተሪ አሸናፊዎች ዝርዝር ይፋ ሲያደርግ የሎተሪው የ4ኛ ዕጣ አሸናፊ የቀድሞ የእግርኳስ ተጫዋች ሸዋረጋ ደስታ አሸናፊ መሆናቸው ታውቋል።

የቀድሞ የባንኮች ተጫዋች የሆነውና በባንክ ማሊያ ብቻ የእግርኳስ ህይወቱን ጀምሮ የጨረሰው ሸዋረጋ ጫማ ከሰቀለ በኋላ የባንኮች ስፖርት ክለብ ስራ አስፈፃሚ እንዲሁን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ አባል የነበረ ሲሆን ሦስት የእግርኳስ መፅሀፎችንም ፅፎ ለአንባቢያን ማቅረቡ አይዘነጋም። ሸዋረጋ በአሁኑ ሰዓት የባንክ የታዳጊዎች ማሰልጠኛ ፕሮጀክት ከፍቶ ከ40 በላይ ታዳጊዎችን እያሰለጠነ የሚገኝ ሲሆን ዕድሉም የእሱ ብቻ እንዳልሆነ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበረው አጠር ያለ ቆይታ አመላክቷል።
“ይሄ የእኔ ዕድል ብቻ አይደለም ፤ የማሳድጋቸው 40 ልጆች ዕድልም ነው።” ያለው ሸዋረጋ በአካዳሚው የሚገኙ ታዳጊዎችን በጎቲያ ካፕ ውድድር ለማሳተፍ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑንና ይህ የገንዘብ ሽልማት መድረሱ አግራሞት እንደፈጠረበት ገልጿል።

“ታዳጊዎቹን ያለምንም የገቢ ምንጭ ነው የማሳድገው። ይህ ለእኔ ትልቅ እድል ነው። ልጆቹ ላይ በደንብ መስራት እፈልጋለው። ባለፈው ከማሳድጋቸው ተጫዋቾች 6 ልጆች ወደ ንግድ ባንክ ቡድን አድገውልኛል። ይህ ትልቅ ነገር ነው።” በማለት ከዕድሉ ጎን ለጎን ስለአካዳሚው የተወሰነ ነገር አካፍሎናል።
ከቀናት በፊት የቆረጡት ሎተሪ መድረሱን ከተቋሙ ሲነገረው አለማመኑንና ሲስተም ላይ በዐይኑ ገብቶ ሲያይ እንደተገረመ ያመላከተው ሸዋረጋ በአራተኛ እጣው መሰረት የ700 ሺ ብር የገንዘብ ተሸላሚ መሆኑን አረጋግጦልናል።

