መቻል ሁለት ተስፋ የተጣለባቸውን ተጫዋቾች አስፈርሟል

በአሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የሚመራው መቻል በዘንድሮ የውድድር ዓመት ለዋንጫው ከታጩ ቡድኖች መካከል አንዱ ሲሆን ከ26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በፊት ከመሪው ሲዳማ ቡና በ11 ነጥቦች ርቆ ተቀምጧል። ቡድኑም ከመሪው ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን ልዩነት ለማጥበብ በዛሬው ዕለት ወሳኝ ጨዋታውን ሀዋሳ ላይ የሚያደርግ ይሆናል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ክለቡ ሁለት ወጣት ተጫዋቾችን ማዘዋወሩ ታውቋል።
ቡድኑን የተቀላቀለው የመጀመሪያው ተጫዋች አንዋር ሙቀዲስ ነው። የጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ፍሬ የሆነው አጥቂው አንዋር ዓምና የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን ዘንድሮም ለቡድኑ 8 ግቦችን አስቆጥሮ በፉክክሩ ደረጃ 2ኛ ላይ ተቀምጧል።
ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ ኝሆኝ ጋት ነው። እንደ አንዋር የጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ውጤት የሆነው የተከላካይ አማካዩ ኝሆኝ በቡድኑ ጥሩ ጊዜን እያሳለፈ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ከቡድን አጋሩ ጋር በመሆን መቻልን ለሁለት ዓመት ተቀላቅሏል።

