መቻል ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሰበትን ሦስት ነጥብ ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ወስዷል

የሁለቱ ቡድኖች ተጠባቂ ጨዋታ በበርካታ የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ድባብ እንዲሁም በቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ እና ዝናብ ታጅቦ ተከናውኗል። በመጀመሪያዎቹ 21 ደቂቃዎችም ሱራፌል ዳኛቸው እና ቻርለስ ሙሴጌ ለቡድን አጋሮቻቸው በፈጠሯቸው ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራዎች እንዲሁም ኮሊንስ ኮፊ እና ቸርነት ጉግሳ ደግሞ የግል ጥረታቸውን ተጠቅመው በሞከሯቸው ኳሶች ግብ ለመቆጠር ተቃርቦ ነበር።
ጥሩ ፉክክር እያሳየ የቀጠለው ጨዋታው 28ኛው ደቂቃ ላይ የሊጉን መሪ የጨዋታው መሪ አድርጓል። በተጠቀሰው ደቂቃም ከቀኝ መስመር መነሻን ያደረገ ኳስ አቤል ያለው ሲሞክር የግብ ዘቡ አሊዮንዚ ናፊያን መልሶት በትክክለኛው ቦታ ላይ የነበረው ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን በጥሩ ቅልጥፍና ግብ አስቆጥሯል።
ግቡ ሲቆጠር እንደታየው ሞቅ ያለ የደጋፊዎች ድባብ ሞቅ ያለ ዝናብ በጨዋታው መዝነብ የጀመረ ቢሆንም የጨዋታው ፉክክር ግን ግለቱን እንደጠበቀ ቀጥሏል። በአንፃራዊነት ወደ ግብ በመድረስ ረገድ የተሻሉት መቻሎች አቤል ያለው ከሞከረባቸው ሌላ የአጋማሹ ሙከራ ውጪ ግባቸውን ሳያስደፍሩ ማጥቃቱ ላይ ትኩረት ሰጥተው ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ለመጫወት ሞክረዋል። በዚህም አብዱልከሪም ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ ፈጥሮ ሳይጠቀምበት ከቀረው አጋጣሚ በመቀጠል ቸርነት ጉግሳ በ41ኛው ደቂቃ ከኮሊንስ ኮፊ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ መቻልን አቻ አድርጓል።

ከዝናቡ ጋር ተያይዞ የመጫወቻ ሜዳው ለጨዋታ ምቹ ያልነበረ ቢሆንም በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ አቤል እና ቸርነት ቡድኖቻቸውን መሪ ለማድረግ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ አድርገው ነበር። ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ወደሜዳ የገባው መቻል ግን በ51ኛው ደቂቃ ውጥኑ እውን ሆኗል። በዚህም ከመዓዘን ምት መነሻን ያደረገ ኳስ የቡድኑ አምበል ግሩም ሀጎስ እንደ ስሙ ግሩም ጎል በግራ እግሩ አስቆጥሯል።
የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደራሳቸው አድርገው መጫወታቸውን የቀጠሉት መቻሎች ጨዋታውን ለመቆጣጠር የፎርሜሽን ለውጥ በማድረግ ቀሪ ደቂቃዎችን ተንቀሳቅሰዋል። ሲዳማዎች በበኩላቸው እንደከዚህ ቀደሞቹ ጨዋታዎች ብልጫ መውሰድ ቀላል ያልሆነላቸው ቢሆንም በተለይ በግራ መስመር በኩል የግብ ምንጭ ለማግኘት ሲሞክሩ ተስተውሏል። በአንፃራዊነት በጨዋታው የመጨረሻ ሩብ ደቂቃዎች ሻል ባለ ፍላጎት ለማጥቃት ሙከራ ቢያደርጉም የጦሩን የኃላ መስመር ሰብሮ መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል። ይባስ በ89ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በገባው በረከት ደስታ ሦስተኛ ግብ አስተናግደው ተሸንፈው ወጥተዋል።

